የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አሸናፊዎች የዶፒንግ ምርመራ ሊደረግላቸዉ ነዉ፡፡
አርትስ 07/03/2011
ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚሰናዳው የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በመጭው እሁድ ህዳር 9 ቀን
2011ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ውድድሩን በማስመልከት በአዘጋጆቹ በኩል መግለጫ ተሰጥቷል፤ በውድድሩ ከ44 ሺ በላይ ተሳታፊዎች
የሚካፈሉ ሲሆን የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አትሌቶች፣ አምባሳደሮች፤ ኢትዮጵያውያን እና
የባህር ማዶ ዜጎች ይታደሙበታል ተብሏል፡፡ በአዘጋጆቹ በኩል አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እንደተደረገም
ተነግሯል፡፡
ዘንድሮ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ምክንያት ከዚህ በፊት የውድድሩ መነሻና መድረሻ
የነበረው መስቀል አደባባይ ተቀይሮ ወደ ስድስት ኪሎ መዛወሩ ተነግሯል፡፡ በዚህም የመሮጫ
አካባቢዎች መነሻውን ስድስት ኪሎ በማድረግ በምኒሊክ ሆስፒታል- ቀበና ድልድይ- እንግሊዝ
ኤምባሲ- ሾላ ገበያ- አድዋ ድልድይ- ላይፕዚግ አደባባይ- ቅዱስ ስላሴ ካቴድራል ቤ/ክርስትያን- 4
ኪሎ- 5 ኪሎ አድርጎ መጨረሻውን በ6ኪሎ በማድረግ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው
ይጠናቀቃል፡፡
በዘንድሮው ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ አትሌቶች ከፀረ- አበረታች መድሀኒት ነጻ መሆናቸው
በምርመራ ይጣራል ተብሏል፡፡
የውድድሩ የክብር እንግዶች ኤርትራዊው አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ እና ዩጋንዳዊው አትሌት ስቲቨን
ኪፕሮቲች ሲሆኑ ከኬንያ፣ ኤርትራ እና ዩጋንዳ የመጡ ተወዳዳሪ አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡
አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተፈጠረው ወዳጅነት ምክንያት በዚህ ሁነት
በክብር በመጋበዙ የተሰማውን ደስታ ገልፆ ለአዘጋጆቹ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ስቴቨን ኪፕሮቲች ለስኬታማነቱ በአንድ ወቅት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የለገሰው ምክር
እንደጠቀመው ተናግሯል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ ውድድሩ በሰላማዊ
ሁኔታ እንዲከናወን ለተሳታፊዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡