loading
የደቡብ ክልልና አዲሱ የሲዳማ ክልል የስልጣን ርክክብ አካሄዱ
የደቡብ ክልል እና አዲሱ የሲዳማ ክልል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ፊት ቀርበው የስልጣን ርክክብ አካሄዱ።

የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ በዛሬው እለት ወስኗል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ጉባኤ የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ የወሰነው የሥልጣን ርክብክብ እንዲደረግ የቀረበለትን አጀንዳ ላይ ከተወያየ በኋላ በማጽደቅ ነው ።

በቀረበው ሰነድ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ርስቱ፥ የሲዳማ ክልል እራሱን ችሎ በመውጣቱ በሌሎች ህዝቦች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

የህዝቦች አብሮነት ከዚህ ቀደምም ለረጅም ዓመታት ተጠናክሮ የቀጠለ ነው ያሉት አቶ እርስቱ ነባሩ ክልል እና አዲሱ ክልል በመደጋገፍ ለጋራ እድገት እንሰራለን ብለዋል።

ውይይቱን ተከትሎም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ዞን በክልል እንዲደራጅ የቀረበለትን አጀንዳ አፅድቋል።

ውሳኔውን ተከትሎ ሲዳማ በሀገሪቱ 10ኛው ክልል የሚሆን ሲሆን፥ የምክር ቤቱ አባላት ለሲዳማ ክልል ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በክልሉ ሌሎች አካባቢዎችም እየተነሱ ያሉ የመዋቅር ጥያቄ በተገቢው መልኩ እንዲታይ መንግስትና የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ።

ከዚህም ሌላ ምክር ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊየን 600 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ላይ በመምከር አጽድቋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *