የጀጎል ግንብ ከንፅህና ጉድለት ጋር በተያያዘ ምክንያት ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 የጀጎል ግንብ ከንፅህና ጉድለት ጋር በተያያዘ ምክንያት ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጀጎል ግንብ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የማስዋብ ስራ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡ “ጀጎልን ጽዱ እና ውብ እናድርጋት” በሚል መሪ ሀሳብ በጀጎል የሚገኙ አሚር ኑር እና አባድር ወረዳዎችን በማስተባበር እና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። የሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ ዳይሬክተር አቶ ጃሚ መሀመድ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የጀጎል ግንብ ለጉዳት እየተዳረገ መምጣቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ጀጎልን ለጎብኚዎች ውብና ምቹ ማድረግ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አንጻር የተጀመረው የንቅናቄ ስራ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ ጀጎልን በማስዋብና ቅርሱን ለትውልድ ለማስተላለፍ ህብረተሰቡ በባለቤትነት መንፈስ መንቀሳቀሱ ስራው በተፈለገው መንገድ እንዲከናወን እያስቻለ ነው ብለዋል።
በጀጎል ውስጥ ከህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ አሁንም ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ በትምህርት ቤቶች በክባባት አማካኝነት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል። ቅርስን ከመጠበቅ፣ ከመንከባከብ እና ከማልማት አንጻር ቢሮው እቅድ አውጥቶ የንቅናቄ ስራዎችን መጀመሩንም አቶ ጃሚ ተናግረዋል። የቅርስ ጥበቃን መሰረት በማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤት እየታየበት በመሆኑ በተለይ ጀጎልን
ጽዱና ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።