loading
የጣሊያን ደርቢ ዛሬ ምሽት በኢንተርና ዩቬንቱስ መካከል ይደረጋል

የጣሊያን ደርቢ ዛሬ ምሽት በኢንተርና ዩቬንቱስ መካከል ይደረጋል

አርትስ ስፖርት 28/03/2011

ባለቤቶቹ Derby d’Italia ይሉታል፤ እኛ ደግሞ የጣሊያን ደርቢ፤ ስያሜው በ1967 በጣሊያናዊው ስፖርት ጋዜጠኛ ጂያኒ ብሬራ ወጥቷል፤ ይህ የእግር ኳስ ጨዋታ ደግሞ በሚላኑ ኢንተርናዚዮናል እና በቱሪኑ ዩቬንቱስ መካከል ይከናወናል፡፡

ቡድኖቹ በሁለቱ የሰሜን ምዕራብ ጣሊያን ታላላቅ ከተሞች ላይ እንደመገኘታቸው መጠን ጉዳዩ ከቅሪላ ማንከባለል የዘለለ የፖለቲካ ተቀናቃኝነት ሰሜት ተላብሶ ሁሌም በጣሊያን እግር ኳስ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የከተሞቹ ተወካይ ክለቦች በአካባቢው የበላይነት ማሳያ ናቸውና፡፡

በተለይ ዩቬ ከሊጉ በካልሽዮፖሊ ቅሌት ዝቅ እንዲል ከተደረገ በኋላ ተቀናቃኝነታቸው ብሷል፤ ክብሩ ዝናው ወደ ኢንተር አጋድሏል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ግንኙነታቸው በጣሊያን እግር ኳስ ሻምፒዮና በ1909 ሲሆኑ ያኔ ዩቬ 2 ለ 0 ረትቷል፤ በአጠቃላይ እስካሁን 238ኛ ጊዜ የተፋለሙ ሲሆን አሮጊቷ 108 ጊዜ የበላይ ናት፤ ዛሬ ምሽት 4፡30 በ15ኛ ሳምንት የጣሊያን ሴሪ ኤ ለ239ኛ ጊዜ የደርቢ ደ ኢታሊያ ጨዋታቸውን በአሊያንዝ ስታዲየም ያደርጋሉ፡፡

አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ከጥቁርና ሰማያዊ ለባሾቹ ቤት ከተለዩ በኋላ ስኬት ወደ ጥቁርና ነጭ ለባሿ አሮጊት አምርታለች፡፡ ዘንድሮም ለተከታታይ ሰባተኛ ጊዜ በሴሪ ኤው ስኬታማ ለመሆን መልካም ጉዞ ላይ ነች፡፡

ሊጉን ዩቬንቱስ በ40 ነጥብ ሲመራ ኢንተር በ29 ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *