loading
የጸጥታው ምክር ቤት የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሰላም እንዲያሰፍኑ ወሰነ

የጸጥታው ምክር ቤት የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሰላም እንዲያሰፍኑ ወሰነ

አርትስ 23/03/2011

የኢፌዴሪ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በቅርቡ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እና ሰብዓዊ ቀውስ አስመልክቶ ሰሞኑን  በጥልቀት መክሯል፡፡

ምክር ቤቱ በአካባቢው የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ጉዳቱን በጥልቀት በመገምገም ከክልሎቹ መንግሥታት ጋር ባደረገው ውይይት የአካባቢውን ሰላም የማስከበር፣ የዜጎችን ህይወት የመታደግ እና በአካባቢው የህግ የበላይነትን በማስከበር አስተማማኝ ሰላም እና ጸጥታን ለማስፈን የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ጣልቃ ገብተው ችግሩን እንዲያረጋጉ ክልሎቹ በጠየቁት መሰረት የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በአካባቢው ተሰማርተው የህግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤትና ንብረታቸው መልሶ በማቋቋምና ሰላም እንዲያሰፍኑ ወስኗል።

በመሆኑም በአካባቢው የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ ይሠራሉ፤ በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ የሚያቀርቡም ይሆናል።

ይህ እርምጃም በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲል ምክር ቤቱ በመግለጫዉ አስታዉቋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ሕልም ዕውን የሚሆነው ሕግና ሥርዓት ሲኖር ነው።

ሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነት ባለበት ሃገር ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ዕድገት ከቶ ሊታሰብ አይቻልም ያለው ምክር ቤቱ ለዚህ እንቅስቃሴ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *