የ2018 ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ዛሬ ይለያል
የ2018 ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ዛሬ ይለያል
አርትስ ስፖርት 30/02/2011
የ2018 ቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ምሽት በቱኒዚያው ኢስፔራንስ ዴ ቱኒስ እና አል አህሊ መካከል በሚደረግ የፍፃሜ ጨዋታ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት አርብ በግብፅ አሌክሳንድሪያ የመጀመሪያ የፍፃሜ ግጥሚያቸውን አድርገው ባለሜዳው አል አህሊ በአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ዋሊድ ሶሊማን (2) እና አምር ኢል ሱላያ ሶስት ግቦች ተጋጣሚውን 3 ለ 1 በመርታት ለሻምፒዮንነት የሚያደርገውን ግስጋሴ አሳምሯል፡፡ ዛሬ ደግሞ በቱኒዚያ መዲና ቱኒስ ላይ በኦለምፒክ ዴ ራዴስ ስታዲየም የመልስ ጨዋታቸውን ምሽት 4፡00 ሰዓት የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡ ይህ ከባድ እና ፈታኝ ጨዋታ በኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ወየሳ ይመራል፡፡ ባለፈው ሳምንት በአልጀሪያዊው ዳኛ አቢድ ሸሪፍ ሜህዲ እየተመራ በተካሄደ የመጀመሪያ ጨዋታ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ የዳኝነት ስርዓት ተግባራዊ የተደረገ ቢሆንም በውዝግብ የተሞላ ነበር፡፡ ውድድሩን አል አህሊ የሚያሸንፍ ከሆነ ለዘጠነኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆን ይችላል፤ አሊያ ኢስፔራንስ ባለድል ከሆነ ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ክብሩን የሚቀዳጅ ይሆናል፡፡ ለ22ኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የውድድሩ አሸናፊ ለሚሆነው ቡድን ዋንጫ እና የ2.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲበረከትለት የፍፃሜ ተፋላሚው ደግሞ 1.25 የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል፡፡