ዩቬንቱስ እና ሮማ ከኮፓ ኢጣሊያ ውድድር ውጭ ሁነዋል
ዩቬንቱስ እና ሮማ ከኮፓ ኢጣሊያ ውድድር ውጭ ሁነዋል
ትናንት ምሽት ሁለት የኮፓ ኢጣሊያ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሲከናወኑ፤ ዩቬንቱስ እና ሮማ ከውድድር ተሰናብተዋል፡፡
ወደ ቤርጋሞ ያቀናው ዩቬንቱስ በአታላንታ የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ኮሎምቢያዊው ዱቫን ዛፓታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ሲያገናኝ፤ ቀሪዋን አንድ ግብ ቲሞቲ ካስታኜ አስቆጥሯል፡፡
የዩቬ ስብስብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ፓውሎ ዲባላን ማካተት ቢችልም ከሽንፈት ሊታደጉት አልቻለም፡፡
አርጊቷ በአሰልጣኝ ማሲሚሊያኖ አሌግሪ ስር እያለች፤ የውድድሩን ዋንጫ አራት ጊዜ ያህል ማሳካት ብትችልም ከዚህኛው የውድድር ዓመት ግን ተሰናብታለች፡፡ ቢያንኮነሪዎቹ በሀገር ቤት ውድድሮች እስካሁን ሽንፈትን የማያውቁ ቢሆንም አልሸነፍ ባይነታቸው በአታላንታ ተገትቷል፡፡
በሌላ ጨዋታ ፊዮረንቲና በአርቴሚዮ ፍራንች የዋና ከተማዋን ቡድን ሮማ አስተናግዶ 7 ለ 1 ረምርሞታል፡፡
የ21 ዓመቱ ጣሊያናዊ አጥቂ ፌዴሪኮ ኬዛ ሀትሪክ ሲሰራ፤ የዲያጎ ሲሞኔ የአብራክ ክፋይ ጆቫኒ ሲሞኔ እንዲሁም ሊዊስ ሙርዬልና ማርኮ ቤናሲ የፍሎረንሱን ቡድን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያሻገሩ ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
አሌክሳንደር ኮላሮቭ ሮማ በባዶ ከመሸነፍ እንዲድን ብቸኛውን ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ ተቀይሮ የገባው ኢዲን ዤኮ ከአርቢትሩ ጋር በገባው እሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡
ፊዮረንቲና በግማሽ ፍፃሜው ከአታላንታ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ማክሰኞ ናፖሊን በፒያቴክ ግቦች አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለው ኤስ ሚላን፤ ዛሬ ምሽት በጁሴፔ ሜዛ ከሚጫወቱት የኢንተር ሚላን እና ላትሲዮ አሸናፊ ጋር በግማሽ ፍፃሜው የሚገናኝ ይሆናል፡፡ ጨዋታው ምሽት 5፡00 ሲል ይከናወናል፡፡