ይህን ክፉ ጊዜ ያለው ለሌለው በማጋራት በመተጋገዝ ልናልፈው ይገባል-አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፡፡
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 ይህን ክፉ ጊዜ ያለው ለሌለው በማጋራት በመተጋገዝ ልናልፈው ይገባል-አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፡፡ ይህን ክፉ ጊዜ ለማለፍ እርሾ ለሚያጥራቸው ጎረቤቶች ያለው ለሌለው በማጋራት ማለፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመኖሪያ አካካቢያቸው ለሚገኙ ከ114 በላይ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የተለያዩ ምግብ ነክ ድጋፎችን አበርክተዋል። አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ችግር በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማለፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ማዕድ በማጋራታቸውም መደሰታቸውን
ገልጸዋል። በዚህ ጊዜ ያለው ለሌለው ማጋራት ትልቅ ሰብዓዊነት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አቅም ያላቸው ወገኖች ሁሉ ድጋፍ ለሚሹ ጎረቤታሞች ማዕድ የማጋራት አገራዊ ጥሪን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥት ባቀረበውና በሕዝቡም ተነሳሽነት በተጠናከረው መደጋገፍ ለጎረቤቶቻቸው ድጋፍ
በማድረጋቸው እርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ከእርሳቸው ጎን ለጎን ለጎረቤቶቻቸው ማዕድ በማጋራት የሚሳተፉ ወገኖችን ሁሉ አመስግነው፤በዚህ
ጊዜ በማዕድ ማጋራት መሳተፍ ቁም ነገር ነው ብለዋል። በቀጣይም መተባበርና መተጋገዙ በሁሉም ከተሞች ክፍለ ከተሞች በሚገኙ አመራሮችና ባለሀብቶች
እንዲጠናከር አቶ ደመቀ ጠይቀዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ኮቪድ 19 ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር መመሪያዎችን የሕይወት መመሪያ በማድረግ ሳይዘናጉ ችግሩን መሻገር ይገባል ብለዋል። በአንድ በኩል እርስ በርስ መተጋገዝ በሌላ በኩል ደግሞ አካላዊ መራራቅን፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን መጠቀም፣ ንጽህና መጠበቅና ሌሎች የመከላከያ ተግባራትን በትከክል መተግበር ከተቻለ ችግሩን በጋራ ማለፍ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ኢዜአ