ጌዲዮን ዘላለም ወደ አሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር አምርቷል፡፡
ጌዲዮን ዘላለም ወደ አሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር አምርቷል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው እግር ኳስ ተጫዋች ጌዲዮን ዘላለም፤ አርሰናልን ተሰናብቶ ወደ አሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር በማቅናት ስፖርቲንግ ካንሳስ ሲቲን ተቀላቅሏል፡፡
ካንሳስ ሲቲ እንዳስታወቀው ጌዲዮን የ2019 የውድድር ዓመት ማብቂያ ድረስ በክለቡ ለመቆየት እንደተስማማ ነው፤ ክለቡ ከፈለገ ውሉን እስከ 2020 እና 2021 ማራዘም እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተገኘውና፤ ውልደቱን ጀርመን ያደረገው የ22 ዓመቱ ጌዲዮን ዘላለም፤ በለጋነቱ ወደ አሜሪካ ሜሪላንድ አቅንቷል፡፡
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እግር ኳስ ወንዶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የርገን ክሊንስማን ከጌዲዮን ጋር ከተወያየ በኋላ ከጀርመን ይልቅ አሜሪካን ወክሎ እንዲጫወት አሳምኖታል፡፡ የአርሰናሉ የቀድሞ አሰልጣኝ ፈረንሳያዊው አርሰን ቪንገርም በተጫዋቹ ችሎታ ተስበው ወደ አርሰናል እንዲመጣ ያደረጉ ሲሆን ያለውን አቅም እንዲያሳድግም አግዘውታል፡፡
አሁን ደግሞ በስፖርቲንግ ካንሳስ አለቃ ፒተር ቬርሜስ ተመራጭ ሁኗል፤ የተጫዋቹ ወደ አሜሪካ መምጣት ሜጀር ሊግ ሶከር ለወጣት ተጫዋቾችም በሩን እየከፈተ እንደሆነ ማመላከቻ እንደሆነ ጠቋሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ ያላቸውን ችሎታ ያሳዩበታል ተብሏል፡፡
‹‹ጌዲዮን ባለ ተሰጥኦ ተጫዋች ነው፤ እኛም ወደ ክለቡ ሲመጣ እንኳን ደህና መጣህ ስንለው ከደስታ ጋር ነው›› ሲሉ ቬርሜስ ተናግረዋል፡፡
‹‹በቀጣይ ሙሉ የውድድር ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ቡድኑ ተወዳዳሪ እንዲሆን ጌዲዮን ከተጫዋቾች ጋር ምን አይነት ቅንጅት መፍጠር እንዳለበት የምንመለከተው ይሆናል›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ተጫዋቹ ከአርሰናልና የአሜሪካ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ጋር ጎልቶ ከታየ በኋላ በጨዋታዎች ላይ ተሰላፊ ለመሆን እየጣረ ነው፡፡ በ2013 የመድፈኞቹን አካዳሚ ከተቀላቀለ በኋላም በቪንገር ስር በአራት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው የመሰለፍ ዕድል ያገኘው፡፡
በውሰት ውል በስኮትላንድ ግላስጎው ሬንጀርስ እና ቪ.ቪ.ቪ ቬንሎ የተሻለ ቢሆንም ያን ያህል ትልቅ የሚባል አልነበረም፤ በዚያ ላይ ጉዳቶች አስቀድሞ ያሳየውን ተሰጥዖ እና የተጠበቀውን ያህል ዕድገት በሰሜን ለንደን አጉልቶ እናዳያወጣ አድርጎታል፡፡
እንደ ኤን.ቢ.ሲ ስፖርትስ ዘገባ በጌዲዮን ዘላለም ተስጥዖ ማንም ጥርጣሬ የሌለው ሲሆን በተለይ እግሩ ከኳስ ጋር ሲገናኝ የሚያሳየው ችሎታ ልዩ ነው፡፡ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመሻገር በሚያደርገው የኳስ ጉዞ ውጤታማ ቢሆንም፤ ከተክለ ሰውነቱ ጋር በተያያዘ ግን አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡
የወጣቱ ተስፈኛ ባለተሰጥኦ ጌዲዮን ዘላለም፤ የሀገረ አሜሪካ የእግር ኳስ የህይወት ጉዞ አልጋ በአልጋ ይሆን… ሜጀር ሊግ ሶከርስ ለጌዲዮን ኮከብነት ማንፀባረቂያ መንገድ ይሆን…?
ስፖርቲንግ ካንሳስ ሲቲ (ስፖርቲንግ ኬ.ሲ) አሜሪካ ሚዙሪ ካንሳስ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ቡድን ሲሆን በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ዌስተርን ኮንፈረንስ ዞን ተሳታፊ ቡድን ነው፡፡
ምንጭ፡- ኤን.ቢ.ሲ ስፖርትስ