ግብፅ የሁለት ሽህ አስራ አንዱን አመፅ የሚዘክሩ ፖለቲከኞችን አሰረች፡፡
ግብፅ የሁለት ሽህ አስራ አንዱን አመፅ የሚዘክሩ ፖለቲከኞችን አሰረች፡፡
የፕሬዝዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ መንግስት በ2011 በግብፅ የነበረውን አብዮት ስምንተኛ ዓመት አክብረዋል ያላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው ፖሊስ ዲግኒቲ የተባለው ፓርቲ አባላል የሆኑትን አሊ አብደል አዚዝ ፋዳሊን በቢሯቸው እንዲሁም የግብፅ ሶሻሊስት ፓርቲ መሪውን ጀማል አብደል ፈታህን በቤታቸው ነው የያዛቸው፡፡
የማህበራዊ ድረ ገፅ አክቲቪስቶች እንዳሉት ፋዳሊ እና አብደልፈታህ በበዓሉ ላይ አልተገኙም፤ ፖሊስም ለምን እንደያዛቸው ማብራሪያ አልሰጠም፡፡
የግብፅ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ በበኩሉ የደህንነት ሰዎች የፈፀሙት ድርጊት ስህተት እና ህገ ወጥ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ግብፅ ከአሁኑ የሰብዓዊ መብት አያያዟ ይልቅ የሙባረክ ዘመን ይሻል ነበር እየተባለች በብዙ ሀገራት ዘንድ የምትታማ ሲሆን ለዚህ መነሻ የሆነው ደግሞ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰሯ ነው፡፡
መንገሻ ዓለሙ