ፍርድ ቤቱ በቡራዩ በተፈጸመው ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ
ፍርድ ቤቱ በቡራዩ በተፈጸመው ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ
አርትስ 22/02/2011
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት በቡራዩ በተፈጸመው ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።
በዛሬው ዕለት ሳምሶን ጥላሁን፣ አለሙ ዋቅቶላ፣ ቡልቻ ታደሰና ሽፈራው አረና ችሎት የቀረቡ ሲሆን፥ ሀሺም አሚርና አሊ ዳንኤል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸዋል።
የፌዴራል መርማሪ ፓሊስ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የ10 ሰዎችን የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ሀሰተኛ ማህተሞችንና ሰነዶችን ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩንና በ17 ባንኮች የገንዘብ ዝውውርማስረጃ ማጠናቀሩን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
መርማሪ ፓሊስ የተጠርጣሪዎች የእርስ በርስ የስልክ ልውውጥ መረጃ ከኢትዮ-ቴሌኮም ማስመጣት፣ ያልተያዙ ግብረ-አበሮችን መያዝ፣ ከብሄራዊ የመረጃ መረብ ደህንነት አገልግሎት ለቴክኒክ ምርመራየተላኩ መረጃዎች መቀበል እና ሌሎች ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማስረጃዎችን ለማጠናቀር ተጨማሪ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የአንደኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው፥ በመርማሪ ፖሊስ እየቀረበ ያለው ማስረጃ ተመሳሳይ ስለሆነ የሚሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አጭር እንዲሆን ጠይቀዋል።
ሌሎች ተጠርጣሪዎችም የዋስትና መብታቸው ተፈቅዶ ክርክሩን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ለፍርድ ቤቱ አስተያታቸውን አቅርበዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤትም ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ባቀረበው የምርመራ ማስረጃ መሰረት ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ የፈቀደ ሲሆን፥ ለህዳር 20 ቀን2011 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ፋና ዘግቧል።