ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በትራምፕ ዘመን የተጣለውን የግሪን ካርድ ክልከላ ህግ ሸረውታል::
አዲስ አበባ፣የካቲት 18፣ 2013 ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በትራምፕ ዘመን የተጣለውን የግሪን ካርድ ክልከላ ህግ ሸረውታል:: ትራምፕ 100 ሺህ 14 በሚል ድንጋጌ ያጸደቁት የቪዛ ክልከላ አዋጅ መነሻው የአሜሪካዊያንን የሥራ እድል ይጋፋል የሚል እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም አዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይህ አዋጅ አሜሪካን የሚጠቅም ሳይሆን የሚጎዳ ነው በማለት በፊርማቸው ሽረውታል፡፡
የባይደን አስተዳደር በዋናነት ህጉን የሻረበትን ምክንያት ሲያብራራ አሜሪካዊያንን ከመጠበቅ ይልቅ ውሃ በማያነሳ ሰበብ ቤተሰቦችን የሚለያይ ነው ብሏል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ትራምፕ ባወጡት ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ ሳቢያ በርካታ ቤተሰቦች ተለያይተው ለመኖር ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በትራምፕ ዘመን የተጣለውን የቪዛ ክልከላ ህግ ጆ ባይደን እንዲሽሩት ወደስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምረው ጥያቄዎች ሲያቀርቡ ነበር፡፡
ባይደን ወደ ነጩ ቤት ከገቡ ወዲህ በርካታ ህጎችን የሻሩ ሲሆን ከተሻሩት ህጎች መካከልም በተወሰኑ የሙስሊም ሀገራት ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳና የሥደተኞች ፖሊሲ ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰነድ አልባ የውጭ ሀገራት ስደተኞች ለዜግነት ጥያቄያቸው መልስ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡