loading
በአፍሪካ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ውድድር ላይ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አቀባበል እና ሽልማት ተበረከተለት

በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ከሚያዝያ 8-12/2011 ዓ.ም በተከናወነው የአፍሪካ ከ – 18 እና ከ – 20 አመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም የእድሜ እርከኖች 82 አትሌቶችን ጨምሮ 111 ልኡካንን በመያዝ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ስድስት ወርቅ ፤ አስር ብር እና አስራ አራት ነሀስ በማምጣት በድምሩ 30 ሜዳሊያዎችን በማሳካት ፤ ከዉድድሩ ተሳታፊ ሀገራት በአጠቃላይ ሜዳሊያ ብዛት 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቋል፡፡

ይህ ልኡክ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሆቴል አቀባበል ሲደረግለት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች እንዲሁም የአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል ።

የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አትሌት ገ/እግዚያብሔር ገ/ማርያም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አሰምተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቶቹ ያገኛችሁት ድል ሊያኩራራችሁ አይገባም፤ በቀጣይ በርትታችሁ መስራት ይኖሩባችኋል፤ ከወዲሁም ለሌሎች ውድድሮች መዘጋጀት አለባችሁ ሲሉ አበርትተዋል፡፡

በአቢጃኑ ውድድር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ውጤታማ ባልሆነችባቸው የርዝመት እና የውርወራ አይነት የሜዳ ተግባር ውድድሮች ላይ ውጤታማ ስትሆን፤ በምትታወቅባቸው የሩጫ ውድድሮች ላይ በኬንያ የበላይነት ተወስዶባታል፡፡

ይህንን ተከትሎ ዶ/ር አሸብር እና አትሌት ገ/እግዚያብሔር ከዚህ ቀደም ውጤታማ ባልሆንባቸው የውድድር ዓይነቶች ድል ማስመዝገባችሁ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በሩጫው ያጣችኋቸው አሉና በቀጣይ ማስተካከል አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ለተሳታፊ ልኡካን ቡድን አባላት የሽልማት እና እውቅና ስነ ስርዓት ተካሂዷል በዚህም፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለወርቅ አሸነፊ አትሌቶች 18 ሺ ብር ፤ ብር ላሳኩ 12 ሺ እንዲሁም ለነሀስ ባለቤቶች 8 ሺ ብር በመስጠት በድምሩ ለቡድኑ 875 ሺ ብር አበርክቷል ።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለልኡካን ቡድኑ አጠቃላይ 450 ሺ ብር ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ ለልኡካን ቡድኑ 165 ሺ በማውጣት ሲሸልሙ፤ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች 10 ሺ: ብር 3 ሺ እንዲሁም ነሀስ 2 ሺ ብር አግኝተዋል ።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *