አስቶን ቪላ ለፍፃሜ ጨዋታ ደርሷል
ኖርዊች እና ሸፊልድ ዩናይትድ በሚቀጥለው ዓመት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ሶስተኛውን ክለብ ለመለየት ደግሞ የቻምፒዮንሽፕ የደርሶ መልስ/play off ጨዋታዎች እየተደረጉ ነው፡፡
የመጀመሪያ ጨዋታዎች ቅዳሜ ዕለት የተደረጉ ሲሆን ትናንት ምሽት አስቶን ቪላ ወደ ፍፃሜው መሻገሩን ሲያረጋግጥ፤ ዛሬ ሌላኛው ቡድን ይታወቃል፡፡
ትናንት ምሽት ዌስት ብሮሚች አልቢዮን በሜዳው ዘ ሀውቶርንስ አስቶን ቪላን አስተናግዶ በክሩግ ዳውሰን ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 ቢረታም፤ በድምር ውጤት 2 ለ 2 መለያየታቸውን ተከትሎ በተሰጠው የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ቪላ 4 ለ 3 በማሸነፍ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በውድድሩ ለፍፃሜ በቅቷል፡፡
ዛሬ ምሽት ደግሞ 3፡45 ላይ የሌላኛው ጨዋታ የመልስ ግጥሚያ ሲደረግ፤ ሊድስ ዩናይትድ ኤላንድ ሮድ ላይ ደርቢ ካውንቲን ይገጥማል፡፡
በመጀመሪያው ግጥሚያ በአሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ የሚመራው ሊድስ ከሜዳው ውጭ በኬማር ሮፍ ብቸኛ ግብ የፍራንክ ላምፓርዱን ደርቢ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
የሊድስና ደርቢ አሸናፊ ዌምብሌይ ላይ በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ከአስቶን ቪላ ጋር ይገናኛል፡፡ ከዚያም ጉዞ ወደ ፕሪምየር ሊግ፡፡