loading
6 ሰዓታትን የፈጀ ስኬታማ ቀዶ ህክምና-በኢትዮጵያ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 19፣ 2013 የልብ የደም ስር ነቅሎ መትከል እና የልብ በር ቀዶ ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መካሄዱን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም ገለጹ፡፡ ቀዶ ህክምናው 6 ሰዓታትን የፈጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ቀዶ ህክምናውን ለየት የሚያደርገው የልብ የደም ስር ነቅሎ መትከል እና የልብን በር ቀዶ ህክምና በአንድ ላይ መደረጉ መሆኑን በጥቁር አንበሳ የልብ ማዕከል የልብ ቀዶ ሐኪም ዶ/ር ፈቀደ አጉዋር ለኢቲቪ ተናግረዋል። ሁለቱ ችግሮች በአንድ ላይ የመከሰታቸው ሁኔታ በጣም አነስተኛ መሆኑን ዶ/ር ፈቀደ ተናግረዋል። የ55 ዓመት እድሜ ያላቸው ታካሚ በግራ በኩል ያለው የልባቸው በር በከፍተኛ ሁኔታ በመጥበቡ እና
ደም አላሳልፍ በማለቱ ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ነበር ብለዋል።

አብዛኛው ጊዜ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የልብ በር መጥበብ እና የልብ ደም ስሮች ሊዘጉ ይችላሉ፤ ይህም በስኳር፣ በደም ግፊት እና በተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮች ሊከሰቱ ይችላል ብለዋል። የቀዶ ህክምናውን ሀላፊነት መውሰድ የሚፈልግና ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለማወቅ የሚከብድ
እንደነበር ሀኪሙ ገልጸዋል። ቀዶ ህክምናው በትላንትናው እለት ከቀኑ 8 ሰዓት ተጀምሮ ምሽት 2 ሰዓት ላይ በስኬት መጠናቀቁን
ዶክተር ፈቀደ ተናግረዋል።

የተዘጋው የልብ የደም ስር በመከፈቱ ደም በአግባቡ ሊተላለፍ ችሏል፤ ውጤቱም እጅግ የተሳካ እና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ነው ብለዋል።
ከቀዶ ህክምናው በኋላ ልብ እና ሳንባ ወደ ቀደመ ስራቸው መመለሱ ለእኛ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል ሲሉ ዶክተሩ ተናግረዋል። ታማሚው በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል። ታካሚው ውጭ ሄዶ ቢታከም እስከ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድረስ ሊያስወጣ እንደሚችል ሀኪሙ
ገልጸዋል። የልብ ቀዶ ህክምናው የተከናወነው ሆሌዜር የልብ ህክምና ማእከል ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *