loading
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ተመረቀ

አርትስ04/02/2011

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች መካከል  የሚገኝና በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገኙት 4 የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ መርቀው ስራ አስጀምረዋል::

ፋብሪካው ከውጭ በተገኘ 8.1 ቢሊዮን ብር ብድር የተገነባ ሲሆን ፤መጋቢት 2008 ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ ተጀምሮ በተሰጠው የጊዜ ገደብ በወቅቱ ያጠናቀቀ መሆኑ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል::

የፋብሪካው የማምረት አቅም በተለይ አገዳ የመፍጨት አቅሙ በቀን 12,000 ቶን ሲሆን፤እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር በቀን ወይም 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በአመት እንደሚያመርት ታውቋል:: 

ፋብሪካው ሙሉ የማምረት አቅም ላይ ሲድርስ ለ12,000 ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ለዚህም ሆነ ለሌሎቹ በአካባቢው ለሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች አገዳ የሚያቀርቡ የመስኖ መሰረተ-ልማት፣የመሬት ልማት ፣የእርሻና የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የጠየቀ ሲሆን ከእርሻውና ተያያዥ ልማቱ ጋር የስራ ዕድል ፈጠራው ከዕጥፍ በላይ እንደሚያድግ ይጠበቃል ያሉትየጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ  አቶ ፍፁም አረጋ ናቸው::

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በበዐሉ ላይ ልምድ ለመውሰድ የተገኙትን የሃገረ ኤርትራ  ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን እንዲሁም የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩ ጊዜ ፕሮጀክቱን በመጠንሰሳቸው በእለቱ የተገኙትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ምስጋና አቅርበውላቸዋል::

የፋብሪካው መመረቅ በአገሪቱ ስኳር የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ 8 እንዲያድግ አድርጓል::

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *