በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የተለያዩ የግብይት ማዕከላት ተገንብተው ተጠናቀቁ
አርትስ 19/02/2011
በሚቀጥለው ወር ከ84 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው 3 የመዲናዋ የግብይት ማዕከላት ወደ ስራ እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ከተማአስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በመዲናዋ 3 ክፍለ ከተሞች የተለያዩ የግብይት ማዕከላት ተገንብተው የተጠናቀቁ ሲሆን፥ በሚቀጥለው ወር ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
በኮልፌ፣ ንፋስ ስልክ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከ84 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከተገነቡት የግብይት ማዕከላት መካከል የኮልፌ እና ንፋስስልክ ክፍለ ከተሞቹ የአትክልት እና ፍራፍሬ ግብይት ስፍራዎች ናቸው።
የአቃቂው ደግሞ የቁም እንስሳት ማዕከል ነው ተብሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የግብይት ተሳትፎ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ አሁንላይ ማዕከላቱን ስራ ለማስጀመር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከላቱ ከ5 መቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን፥ የቁም እንስሳት ማዕከሉ ደግሞ በአንድ ጊዜ 5 ሺህ ያህልእንስሳትን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ወደ ማዕከላቱ ገብተው ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ልየታ እየተከናወነ ሲሆን፥ በስራው ላይ የሚሰማሩ ዜጎች የብድር አቅርቦት የሚያገኙበትንሁኔታ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
በዚሁ ዓመትም ሌሎች ተመሳሳይ ማዕከላትን በሌሎች ክፍለ ከተሞች ለማስገንባት ዲዛይን የማውጣት ስራ እየተከናዎነ መሆኑም አስረድተዋል። ኤፍ ቢ ሲ