loading
ግብፅና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ ካርቱም ላይ ይመክራሉ

አርትስ 18/04/2011

ካርቱም ላይ በሚካሄደው በዚህ ስብሰባ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የደህንነት ሀላፊዎች ናቸው ተገናኝተው የሚወያዩት፡፡

የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር እና የግብፁ አቻቸው አብደልፈታህ አልሲሲ በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ባደረጉት የጎንዮሽ ስብሰባ ነበር ለዛሬው ውይይት ቀጠሮ የያዙት፡፡

ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው ሁለቱ ሀገራት በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚወያዩ ሲሆን በካርቱምና በካይሮ መካል ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ለማርገብም በስፋት ይመክራሉ ተብሏል፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሱዳን እና ግብፅ በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባት ውስጥ ሲገቡ ታይተዋል ፡፡

ግብፅ  የሱዳን እና የቱርክ ግንኙነት ጥቅሜን ይጎዳል ስትል ሱዳን በበኩሏ የአልሲሲ መንግስት ከኤርትራ ጋር ተቃዋሚዎችን በመደገፍ በከሰላ በኩል ጥቃት እንዲሰነዘርብን ተንቀሳቅሷል በማለት ስትከስ ነበር፡፡

ይሁን እና አሁን ላይ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ባደረጓቸው ተከታታይ ውይይቶች መልካም ወደሚባል ደረጃ መሸጋገሩ ይነገራል፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባቢከር ሲዲጅ እንዳሉት የካርቱሙ ውይይት ሁለተኛ ዙር በመጭው የካቲት ወር ካይሮ ላይ ይካሄዳል፤ ካርቱም ላይ የተወያዩበት ጉዳይ የት እንደደረሰም ውጤቱ ይለካል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *