የቀድሞው የቻይና ምክትል የደህንነት ኃላፊ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው
የቀድሞው የቻይና ምክትል የደህንነት ኃላፊ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው
አርትስ ታህሳስ 19 2011
የቀድሞው የቻይና ምክትል የደህንነት ኃለፊ ማ ጀይን ስልጣንን በመጠቀም የዉስጥ ለዉስጥ ንግድ በመፈፀም በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በሀገሪቱ ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንደተበየነባቸው ተነግሯል፡፡
ሳዉዝ ቻይና ሞርኒንግ እንደዘገበው ወንጀልን መፈፀማቸዉን ያመኑት ማ ጀይን ከ30 አመታት በላይ በቻይና የስለላ ወኪል ዉስጥ የሰሩ ሲሆን በአዉሮፓዉያኑ ቀመር ከ2006 ጀምሮ ደግሞ በደህንነት መስሪያ ቤት ዉስጥ ምክትል ሚኒስትር ሆነዉም አገልግለዋል፡፡
የሃገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ ዮንጋካንግ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2015 እድሜ ልክ እስራት ከተወሰነባቸው በኋላ ማ ጀይን በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተወሰነባቸው ከፍተኛው ባለስልጣናት ናቸው ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪው ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የፓለቲካ ስልጣናቸውን ለግል ጥቅም በማዋልና ሙስና በመቀበል በተጠረጠሩበት ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት እንደተወሰነባቸው የተገለጸ ሲሆን ከእስራቱ በተጨማሪም 7 ሚሊዮን 260 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ለ30 ዓመታት ያህል በደህንነት መዋቅሩ ያገለገሉት ማ ጀይን በ2015 በሙስና ተጠርጠረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መባረራቸውም ይነገራል፡፡
ፕሬዚዳት ሺ ጂፒንግ በ2012 ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ በርካታ ባለስልጣናት ከሙስና ጋር የተያያዘ ምርመራ እንዲደረግባቸው ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የአልጀዚራ ዘገባ ያስረዳል፡፡