loading
ሳላህ የካፍ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ክብርን በድጋሜ ተቀዳጀ

ሳላህ የካፍ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ክብርን በድጋሜ ተቀዳጀ

ትናንት ምሽት በሴኔጋሏ መዲና ዳካር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የ2018 የኮከቦች የሽልማት ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

በዚህም በወንዶች ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ መሀመድ ሳላህ፤ የክለብ አጋሩን ሴኔጋላዊውን ሳዲዮ ማኔና ጋናዊውን ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ በመብለጥ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጧል፡፡

ሳላህ ይሄንን ክብር ለተከታታይ ሁለት አማታት ሲያሸንፍ ሽልማቱን ከቀድሞው ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋችና ከላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ እጅ ተቀብሏል፡፡

ተጫዋቹ በ2017- 2018 የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች 44 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ ከሊቨርፑል ጋር የቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ ነበር፡፡

መሀመድ ሳላህ ባደረገው ንግግር ‹‹ ከህፃንቴ ጀምሮ ይሄንን ሽልማት ለማሸነፍ ሳልም ነው የኖርኩት፤ አሁን ደግሞ በተከታታይ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ አሳክቸዋለሁ›› ብሏል፡፡

በሴቶች ደቡብ አፍሪካዊቷ ቴምቢ ክጋትላና ኮከብ ተብላለች፡፡

በሌሎች የሽልማት ዘርፎች የሞሮኮውና የዶርትሙንዱ አሽራፍ ሀኪሚ የዓመቱ ወጣት ተጫዋች፤ በወንዶች ኮከብ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ፤ በሴቶች ዴሲሪ ኤሊስ ከደቡብ አፍሪካ ኮከብ ሲባሉ የሞሪታኒያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን እና የናይጀሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓመቱ ኮከብ ቡድኖች ተሰኝተዋል፡፡

የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የመጀመሪያውን የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች ሽልማትን ደግሞ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፎዚ ሌክጃ አሸንፈዋል፡፡

የዩጋንዳው ዴኒስ ኦኒያንጎ፣ የአይቮሪ ኮስቱ ሰርጌ ኡርዬ፣ የሞሮኮው ሜህዲ ቤናሽያ፣ የአይቮሪ ኮቱ ኢሪክ ቤይሊ፣ ሴኔጋላዊው ካሊዱ ኩሊባሊ፣ የጊኒው ናቢ ኬይታ፣ የጋናው ቶማስ ፓርቴ፣ የአልጀሪያው ሪያድ ማህሬዝ፣ ግብፃዊው መሀመድ ሳላህ፣ ጋቦናዊው ኦባማያንግ፣ እና ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ምርጥ 11 ውስጥ ተካትተዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *