loading
የዚምባቡዌው ፓስተር  የ20 ዓመት የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ::

የዚምባቡዌው ፓስተር  የ20 ዓመት የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ

ፓስተር እና አክቲቪስት ኢቫን ማዋሪሬ የዚምባቡዌ ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄያቸውን ሊያይላቸው ይዞት የነበረው ቀጠሮ ተራዝሟል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቱ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክርክሩን ለማድረግ ዝግጁ ሆኖ ሳይገኝ በመቅረቱ ነው፡፡

ፓስተሩ የታሰሩት የኤመርሰን ምናንጋግዋ መንገስት እንዲዳከም በሚያደርግ አመፅ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ነው፡፡

ማዋሪሬ በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው ካገኛቸው እስከ 20 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት  ሊፈርድባቸው እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡

አክቲቪስቱ ፓስተር እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2016 በወቅቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ላይ  በድፍረት ሀይለኛ ትችት  ካቀረቡ ወዲህ እውቅናቸው ከፍ ብሏል ፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ከአክቲቪስቱ በተጨማሪ በዚምባቡዌ በነዳጂ ዋጋ መጨመር ምክንያት በተቀሰቀሰው አመፅ ተሳትፈዋል የተባሉ 600 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን የዋስትና መብታቸው እንዳይከበር ፍርድ ቤቱ ከልክሏል፡፡

መንግስት ያቋቋማቸው የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሀገሪቱ ጦር አባላት እና የፀጥታ ሀይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ያልተመጣጠነ ሀይል ተጠቅመዋል የሚል ክስ አቅርበዋል፡፡

እስካሁን በአመፁ ምክንያት ስምንት ሰዎች መገደላቸውንም ተቋመቱ ባቀረቡት ሪፖርት ይፋ አድርገዋል ፡፡

ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በሀገራቸው አመፅ በመስፋፋቱ ምክንያት ከሩሲያ ጉብኝት በኋላ በዳቮሱ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ለመሳተፍ የያዙትን እቅድ  ሰርዘው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡

 

 

 

መንገሻ ዓለሙ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *