loading
የ12ኛ ሳምንት መርሀግብር የማጠናቀቂያ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ

የ12ኛ ሳምንት መርሀግብር የማጠናቀቂያ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ

በሊጉ የ12ኛ ሳምንት ትናንት ሶስት ያህል ግጥሚያዎች በክልል ስታዲየሞች ሲከናወኑ፤ በጉጉት በተጠበቀው የአማራ ደርቢ (የወንድማማቾች ደርቢ) ባህር ዳር ከነማ ከፋሲል ከነማ ያለግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

አዳማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 1 ለ 0 እንዲሁም በደቡብ ደርቢ ሃዋሳ ከነማ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስን 3 ለ 2 ድል አድርገዋል፡፡

ዛሬ አዲስ አበባ እና ጅማ ላይ ሁለት ጨዋታዎች ይከናውናሉ፤ በካፍ ውድድሮች ተሳታፊ የነበረው ጂማ አባ ጅፋር  በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በሞሮኮው ቡድን ከተሰናበተ በኋላ የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ጅማ ላይ ያደርጋል፡፡

ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር 9፡00 ሲል የደቡቡን ተወካይ ወላይታ ድቻ ያስተናግዳል፡፡ ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ሳይጨምር 5 ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉት፡፡

ሌላኛው ግጥሚያ 11፡00 ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢትን ያስተናግዳል፡፡

ደደቢት መቀመጫውን ከቀየረ በኋላ፤ ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ  ጊዜ ይገናኛሉ፡፡ ፈረሰኞቹ በተከታታይ ድል በማድረግ ወደ መሪዎቹ ተርታ እየተሰለፉ ሲሆን በአንፃሩ ደደቢት ኮከቦችን ለተቀናቃኞቹ አሳልፎ በመስጠት በወጣት ተጫዋቾች እየተካፈለ ይገኛል፤ በሊጉም ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡

ጊዮርጊስ ድል የሚያደርግ ከሆነ በ21 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ሁለተኛ ላይ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥቦች ሊጉን ሲመራ፤ ሀዋሳ እና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 20 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ ፋሲል ከነማ በ19፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ በ18 ነጥቦች ከአራት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ተቆናጥጠዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *