loading
ቼልሲ የካራባዎ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚነቱን አረጋግጧል

ቼልሲ የካራባዎ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚነቱን አረጋግጧል

የ2018/19 የእንግሊዝ ፉትቦል ሊግ ካፕ (ካራባዎ ዋንጫ) የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ግጥሚያ ትናንት ምሽት ተካሂዷል፡፡

ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ ጨዋታቸውን ያከናወኑት ቼልሲ እና ቶተንሃም ሲሆኑ ሙሉ ጨዋታው በሰማያዊዎቹ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ ውጤት 2 ለ 2 ሲለያዩ በተሰጠው የፍፁም ቅጣት መለያ ምት የማሪዚዮ ሳሪው ቡድን በ4 ለ 2 ውጤት ድል አድርጓል፡፡

ባለሜዳዎቹ ቼልሲ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ንጎሎ ካንቴ እና ኢደን ሃዛርድ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2 ለ 0 መምራት ችለው ነበር፤ ነገር ግን ከዳኒ ሮዝ የተሸገረለትን ኳስ ፈርናንዶ ሎሬንቴ በሁለተኛው አጋማሸ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ለስፐርሶች አስቆጥሮ ቡድኑን በድምር ውጤት አቻ ማድረግ ችሏል፤ በቀሪዎቹ የጨዋታ ክፍል ግን ሌላ ተጨማሪ ግብ ከመረብ ማገናኘት አልቻሉም፡፡

በሌሎች የእግር ኳስ ውድድሮች የሚሰራው ከሜዳው ውጭ ግብ ያስቆጠረ ቡድን አላፊ ይሆናል የሚለው ህግ፤ እዚህ ላይ የማይሰራ በመሆኑ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት ሂደት አምርተዋል፡፡

በፍፁም ቅጣት ምቱ ከተሳተፉት ተጫዋቾች በቼልሲ በኩል ዊሊያን፣ አዝፒሊኮይታ፣ ጆርጊንሆ እና ሊዩዝ ሲያስቆጥሩ፤ በስፐርስ በኩል ኢሪክሰንና ላሜላ ቢያስቆጥሩም፤ ኢሪክ ዳዬር እና ሉካስ ሞራ አምክነዋል፡፡

ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ በዚህ ጨዋታ ላይ የሃሪ ኬን፣ ደል አሊ እና ሰን ሁንግ ሚንን አገልግሎት  አለማግኘታቸው  ጎድቷቸዋል፡፡

ቼልሲ ለፍፃሜ ጨዋታው ከፔፕ ጓርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ቡድኑ በ16 ዓመታት ውስጥ በሁሉም ውድድሮች በ15 የፍፃሜ ጨዋታ ላይ መድረስ ችሏል፡፡

አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ ቡድናቸው  በፕሪምየር ሊጉ፤ በአርሰናል ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ  ተጫዋቾቻቸውን ለማነቃቃት እንደተቸገሩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን ከዚህኛው ድል በኋላ ግን ከተጫዋቾቻቸው ጋር ደስታቸውን አክብረዋል፡፡

የፍፃሜው ጨዋታ ዊምብሌ ላይ ከአንድ ወር በኋላ ይከናወናል ተብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *