loading
የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ ታይላንድን ተጫዋቼን በ10 ሺ ዶላር  ቀይሪኝ እያለ ነው

የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ ታይላንድን ተጫዋቼን በ10 ሺ ዶላር  ቀይሪኝ እያለ ነው

ፌዴሬሽኑ የባህሪን ስደተኛ እግር ኳስ ተጫዋቼን ሃኪም አል- አራይቢን ከዕስር ፍቱት ሲል የ10 ሺ ዶላር ገንዘብ በማቅረብ ጥያቄውን ለታይላንድ መንግስት ማቅረቡን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

አል አይራቢ በአውስትራሊያ ጥገኝነት ከጠየቀ በኋላ ለአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን በታይላንድ ከባለቤቱ ጋር የጫጉላ ሽርሽር እያሳለፈ በነበረበት ወቅት በታይላድ ፖሊሶች ከተያዘ ሰነባብቷል፡፡

ተጫዋቹ በባህሪን መንግስት በጥብቅ የሚፈለግ ሲሆን በፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥፋት ፈፅመሀል በሚል ክስ በሌለበት የ10 ዓመት ዕስራት ተፈርዶበታል፡፡

የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አል- አራይቢ በፍጥነት ወደ አውስትራሊያ መመለስ እንዳለበት ማሳሳቢያ ልኳል፡፡

አል- አራይቢ ደግሞ ከወንጀሉ ንፁህ እንደሆነና ባህሪን ውስጥ ባለው የፖለቲካ አቋም ክፉኛ እንደተሰቃዬ ተናግሯል፡፡ ሰኞ ዕለት ባንኮክ የሚገኘውን ፍርድ ቤትም ለእናት ሀገሩ ባህሪን አሳልፎ እንዳይሰጠው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተጫዋቹን የታይላንድ ቆይታ በ60 ቀናት ያራዘመ ሲሆን በቆይታውም ወደ ባህሪን ተመልሶ እንዳይላክ የሚያጠይቀውን ተቃውሞ ማስገባት እንደሚችል ተነግሮታል፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቪድ ጋሎፕ ‹‹ሃኪም አል- አራይቢ በአውስትራሊያ ቋሚ ነዋሪ መሆኑንና በፓስኮ ቫሌ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አል-አራይቢ ወደ አውስትራሊያ የተሰደደው በ2014 ሲሆን ፖለቲካዊ ጥገኝነት በ2017 ጠይቆ በሜልቦርኑ ፓስኮ ቫሌ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

የባህሪን የመብቶችና ዴሞክራሲ ኢንስቲቲዩት ደግሞ በከፈተው ዘመቻ ወደ ሀገሩ የሚላክ ከሆነ ስቃይ እንደሚደርሰበት በመግለፅ አጋርነቱን ለእግር ኳስ ተጫዋቹ አሳይቷል፡፡

ሃኪም አል-አራይቢ ከባለቤቱ ጋር የጫጉላ ሽርሽር ጊዜውን እያሳለፈ በነበረበት ወቅት ባለስልጣናት ከባንኮክ አየር ማረፊያ በ2018 በወርሀ ህዳር እንደተያዘ ተነግሯል፡፡

የተጫዋቹን መያዝ ተከትሎ በርካቶች ድምፃቸውን እያሰሙ ሲሆን የአውስትራሊያ መንግስት፣ የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል /ፊፋ/ እና የዓለም ዓቀፍ ተጫዋቾች ህብረት ተጫዋቹ እንዲለቀቅ እየተከራከሩ ነው፡፡

የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአውስትራሊያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር በመመካከር ሃኪም አል-አራይቢን እናድን ለሚለው ዘመቻ እንዲያግዝ 10 ሺ ዶላር እያሰባሰበ ይገኛል፡፡

እንደ ጋሎፕ ገለፃ ባለፈው የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለሃኪም የሚደረገው ድጋፍ ከፍ ወደአለ ደረጃ መሸጋገሩን ነው፡፡

‹‹በአውስትራሊያ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ሀኪም እንዲለቀቅ ድጋፋቸውን አጠንክረዋል ያሉት ስራ አስፈፃሚው፤ ይህ የብዙሃኑ ድጋፍ መቀጠል አለበት›› ብለዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *