የኢራን ፕሬዚዳንት አሜሪካ በምታደርገው ምርጫ ሀገራቸው መደራደሪያ ሆና አትቀርብም አሉ ፡፡
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2013 የኢራን ፕሬዚዳንት አሜሪካ በምታደርገው ምርጫ ሀገራቸው መደራደሪያ ሆና አትቀርብም አሉ ፡፡የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ በቨርቹዋል በተካሄደው 75ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢራን በአሜሪካ ምርጫም ሆነ በውስጥ ጉዳይ ላይ በጭራሽ መደራደሪያ ሆና አትቀርብም ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የሀገራችን ክብርና ብልጽግና ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊያችን ነው ያሉ ሲሆን ኢራን በጭራሽ ለአሜሪካ ምርጫም የውስጥ ጉዳይ መደራደሪያ ሆና አትቀርብም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡አሜሪካ ከድርድርም ከጦርነትም ነጻ የሆነ ጫና እያሳደረችብን ነው ያሉት ሮሃኒ ህይወት በማዕቀብ ውስጥ ፈጣኝ ቢሆንም ያለነጻነት ያለው ህይወት ግን በእጅጉ የከበደ ነው ብለዋል፡፡
ሮሃኒ አሁን ጊዜው ማንኛውንም ጫና እምቢ የምልበት ጊዜ ነው በሌሎች እጅ የሚጠመዘዝበት ዘመን ማብቃት ይገባዋል በመሆኑም ሀገራችንና ተተኪ ትውልዱ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዓለም ይገባቸዋል ባይ ናቸው፡፡በቅርቡ አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ አዲስ ማዕቀቦችን መጣሏ የሚታወቅ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከአባል ሀገራቱ ተቃውሞ መግጠሙን ሽኑዋ ዘግቧል፡፡