ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው::
ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ መሆኑን የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከአሥሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በሀብት ምዝገባ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።በዚህም በተቀመጠው መደበኛ የሀብት ማስመዝገቢያ ጊዜ ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት በአምስት ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የጊዜ ገደብ መቀመጡ ተገልጿል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ወዶ አጦ እንደገለጹት ከአሥሩ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል በጊዜ ገደቡ ሀብታቸውን ያስመዘገቡት የቦሌ፣ የአራዳ እና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ብቻ ናቸው። በመሆኑም “ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ከመስከረም18 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተሻሻለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2013 መሠረት ለኮሚሽኑ የእንድ ሺህ ብር ቅጣት በመክፈል የሀብት ማስመዝገብ ግዴታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል” ብለዋል።
በኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ በበኩላቸው አመራሮቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብታቸውን በማስመዝገብ ግዴታቸውን የማይወጡ ከሆነ ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ጉዳዩን አግባብነት ላለው የምርመራ አካል ያስተላልፋል።