ክሬት በተባለችው የግሪክ ደሴት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በንብረት ላይ ትልቅ ውድመት አደረሰ::
አዲስ አበባ፣ ህዳር 02፣ 2013 ክሬት በተባለችው የግሪክ ደሴት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በንብረት ላይ ትልቅ ውድመት አደረሰ:: የደሴቷ ባለ ስልጣናት እንዳሉት የመንገድ አውታሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአደጋው ወድመዋል፡፡ ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ጎርፉ በርካታ ቤቶችን ከማጥለቅለቁ በሻገር ተሸከርካሪዎችን ወደ በባህር ሲወስዳቸው ታይቷል፡፡
ጎርፉ በርካታ የመሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት ቢያደርስም እስካሁን በሰው ህይዎት ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ አልተሰማም፡፡ የደሴቷ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በጎርፉ ተከበውና መወጫ አጥተው ለአደጋ ሊጋለጡ የነበሩ ስምንት ሰዎችን ማዳናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጎርፉ የተከሰተው በደሴቷ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ሲሆን ዝናቡ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡
አደጋው በተባባሰባቸው አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ነዋሪዎችም ከመንግስት መመሪያ እስኪሰጣቸው ድረስ በቤት ወስጥ እንዲቆዩ ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ግሪክ ከአንድ ወር ባለሰ ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደዚህ አይነት ከባደ የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥማት ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡