በሱዳን በተለያዩ ከተሞች በኑሮ ውድነት ሳቢያ አዲስ ተቃውሞ መቀስሰቀሱ ተሰማ::
አዲስ አበባ፣የካቲት 3፣ 2013 በሱዳን በተለያዩ ከተሞች በኑሮ ውድነት ሳቢያ አዲስ ተቃውሞ መቀስሰቀሱ ተሰማ:: ተቃውሞው የተቀሰቀሰው በዳርፉር ግዛት በሚገኙ ከተሞች ሲሆን በሰልፉ የተሳተፉት በአብዛኛው ወጣቶች መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በኑሮ ውድነት ሳቢያ ለርሃብ መጋለጣቸውን የሚገልፁ ጥያቄዎችን ይዘው ነው ጎዳና የወጡት፡፡
በደቡብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኒያላ ለተቃውሞ የወጡት ወጣቶች ሊበትኗቸው በሞከሩ የፀጥታ ሃሎች ላይ ድንጋይ ይወረውሩ እንደነበር ዘገባው የዓይን እማኞችን ጠቅሶ አትቷል፡፡ በቀይ ባህር በምትገኘው ፖርት ሱዳን ከተማም ተማሪዎች አመፅ በማንሳታቸው መክንያት ትምህርት ቤቶችና በርካታ የንግድ ሱቆች መዘጋታቸውን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ሱና ዘግቧል፡፡
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ በደቡብ ኮርዶፋና ገዳሪፍ አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች ተከስተው ዝርፊያዎችና የንብረት መውደም ደርሷል ነው የተባለው፡፡ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በኑሮ ውድነት ሳቢያ የተጀመረ አመፅ ወደ ፖለቲካዊ ይዘት ተሸጋግሮ ከስልጣን እንዳስወገዳቸው ይታወሳል፡፡