loading
ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ::

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2013 ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ:: ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ለፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እንዲሁም ለትራፊክ ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት አባላት የአደጋውን ምክንያት ለመቀነስ የሚያስችል ስልጠና መሰጠት ጀምሯል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአለም ላይ በየአመቱ በአማካይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ።በኢትዮጵያም በመንገድ ትራፊክ አደጋ ሳቢያ በየእለቱ በአማካይ 11 ሰዎች ለህልፈት ይዳረጋሉ፤ በ2012 በጀት አመት ብቻ 4 ሺህ 133 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።በበጀት ዓመቱ በ12 ሺህ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን 9 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል።

በትራንስፖርት ሚንስቴር የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ኢንጅነር ሰመረ ጅላሉ እንዳሉት ከሚፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ አይነተኛ ምክንያት ሆኗል።ለብዙዎች ሞትና አካል ጉዳት መንስኤ መሆኑንም አብራርተዋል።የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ትኩረት የተደረገው ደህነንነቱ የተጠበቀ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገድ ማዘጋጀት ላይ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ የፍጥነት ገደብ የዚሁ አካል እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።የቁጥጥር ስራዎች ስኬታማ ለማድረግ ከብሉምበርግኢኒሼቲቭ ፎር ግሎባል ሴፍቲ ጋር የአቅም ግንባታ
ስልጠና መጀመሩን ገልጸዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *