የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ምርጫው በስድስት ወር እንዲራዘም ጠየቀ::
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2013 የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ምርጫው በስድስት ወር እንዲራዘም ጠየቀ:: በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም ተብለው ፈቃዳቸው ከተሰረዙ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ፓርቲ መጪው ብሔራዊ ምርጫ በስድስት ወር እንዲራዘም ጠየቀ። የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ-ገዳ ቢሊሱማ ከምርጫ ቦርድ ጋር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያካሄድ በነበረው ክርክር ፈቃዱ መሰረዙ ትክክል እንዳልሆነ እንደተወሰነለት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ ታደሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ሮበሌ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርግ መቆየታቸውን እና ጠቅላይ ፍርድ ቤትም መሰረዙ ትክክል አይደለም ሲል መወሰኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።በምርጫ ቦርድ ምክንያት ከምርጫ ውጪ ሆነናል" የሚሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ፣ መጪው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በስድስት ወር ተራዝሞ መስከረም 2014ዓ.ም እንዲካሄድ ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲያቸው ስም ከገዳ ፓርቲ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ-ገዳ ቢሊሱማ በሚል መቀየራቸውን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ደንብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ስርዓት ቁጥር 1162/2011 መሰረት በማድረግ በአገሪቱ በምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ድጋሚ ምዝገባ እንዲያከናውኑ መደረጉ ይታወሳል።