loading
የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ቅሬታ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ገለፀ ፡፡ የኢ/ያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 19 ባደረገው 7ኛ መደበኛ ጠቅላላ ስብሰባ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ የማራቶን ተወዳዳሪ አትሌቶች በኑከራ ውድድር መምረጥ አስፈላጊ በመሆኑና በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ በአሰልጣኞችና በአትሌቶቹም ጭምር በጋራ በተደረገ በመሆኑ እንድትሳተፉ ሲል በወንዶች የ12 እንዲሁም በሴቶች የ8 አትሌቶች ስም ዝርዝር ይፋ በማድረግ በመጪው ቅዳሜ በሰበታ የመምረጫ ውድድር ላይ እንዲገኙ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይሁን እንጂ በወንዶቹ ጥሪ ከተደረገላቸው አትሌቶች አንዱ የሆነው እና ኢትዮጵያን በተለያዩ መድረኮች ያስጠራው ቀነኒሳ በቀለ አስቀድሞ በመጣሪያው የማይወዳደርባቸውን ምክንያት በመጥቀስ እንደማይካፈል የቕሬታ ደብዳቤውን ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል፡፡ ቀነኒሳ ባስገባው የቅሬታ ደብዳቤ ከአምስት ዓመት በፊት በብራዚሉ የሪዮ ኦሊምፒክ ሀገሩን በማራቶን ወክሎ እንዳይሳተፍ እና ከውድድሩ እንዲቀር መደረጉን አስታውሶ ከባለፈው ዓመት ወደ ዘንድሮ
እንዲተላለፍ በተደረገው የኦሊምፒክ መድረክ ጥሪ ሰዓት ስለነበረው በወቅቱ ምርጫ ተካትቶ እንደነበርና ልምምድ ላይ እንደነበር አስታውቋል፡፡

በኮቪድ 19 ምክንያት ከተራዘመ በኋላ ቀደም ሲል ይመረጥበት የነበረው በዓለም አቀፍ ውድድር ጥሩ ሰዓት ማስመዝገብ የሚለው ህግ በማስቀረት በሀገር ውስጥ የማራቶን ማጣሪያ ውድድር እንዲደረግ ፌዴሬሽኑ አዲስ ህግ ያወጣ መሆኑን ገልጧል፡፡ በዚህ የማጣሪያ ውድድር ላይ የብቃት ማነስ ጉዳይ ሳይሆን ወቅቱን ያልጠበቀ፣ የውድድር ጊዜው በጣም የቐረበና አትሌቱን ጉዳት ላይ የሚጥል በመሆኑ እንዳላመነበት በመጥቀስ እንደማይሳተፍ
አስታውቋል፡፡

ቀነኒሳ በማራቶን ያስመዘገበው ሰዓት ከሌሎች የሐገር ቤት አትሌቶች በአንድ ደቂቃ የሚበልጥ መሆኑን በመጥቀስ በውድድሩ የማልሳተፍ መሆኑ ታውቆ በቀጥታ ሀገሬን እንድወክል እንድመረጥ ይደረግ ሲል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከምንጊዜውም በላይ በሙሉ ጤንነትና ብቃት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልፆ ይህንን ብቃቱን ወደፊት በሚደረጉ ውድደሮች ላይ የሚያሳይ መሆኑን ገልጧል፡፡ ከቀነኒሳ በተጨማሪ በሁለቱም ፆታዎች ውስን የታጩ አትሌቶች በዚህ ማጣሪያ እንደማይካፈሉ እየገለፁ መሆናቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *