loading
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተጠራው የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም በኛ በኩል እውቅና አልነበረውም አሉ::

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተጠራው የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም በኛ በኩል እውቅና አልነበረውም አሉ:: ተቀዳሚ ሙፍቲው ይህን ያሉት የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ በመልዕክታቸው በዓሉ በሰላም እንዲጠናቅ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣምጠይቀዋል።

ሀገሪቱ የተደቀነባትን የሰላም እጦት በጋራ ለመሻገር በአንድነት መቆምና ወደ ፈጣሪ መቅረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዓሉ በአደባባይ የሚከበር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሮናቫይረስ የጥንቃቄ መንገዶች ሳይዘነጉ በዓሉ እንዲከናወንም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ የዛሬውን የአዲስ አበባ የአደባባይ ፊጥራ በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መመካከራቸውን ያወሱት ሐጅ ኡመር ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተጠራው የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም በኛ በኩል እውቅና አልነበረውም ነው ያሉት፡፡

የዛሬውን የጎዳና ላይ አፍጥር በተመለከተ ግን የተሳካ እንዲሆን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው “እለቱም የኛ አብሮነት እና ወንድማማችነት ጎልቶ የሚታይበት እንዲሆን ሁሉም ለጋራ ስኬቱ በጋራ መቆም አለበት” ብለዋል። ተቀዳሚ ሙፍቲው ባስተላለፉት መልእክት በጾም ፍች ወቅት አቅመ ደካሞችንና ህመምተኞችን መጠየቅ ሃይማኖቱ ስለሚያዘን ተግባራዊ ማድረግ አለብን ብለዋል። በዓሉ ዛሬ ማታ ጨረቃ ከታየች በ29ኛው ቀን ረቡዕ ይሆናል፤ ዛሬ ማታ ካልታየች ግን በዓሉ ሐሙስ እንደሚሆን ነው ሐጅ ሙፍቲ በመግለጫቸው ያስታወቁት።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *