loading
የግብፅ የአፍሪካ የክትባት ምርት ማዕከል የመሆን ዕቅድ::

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16፣ 2013  ግብፅ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በማምረት የአፍሪካ ማዕከል የመሆን ፍላጎት አለኝ አለች ካይሮ በሶስት ሳምንታት ውስጥ 2 ሚሊዮን የሲኖቫክ ክትባት ለማምረት መዘጋጀቷን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሃላ ዛይድ ተናግረዋል፡፡ ቫሴራ በመባል የሚታወቀው የግብፅ ክትባት አምራች ኩባንያ በቻይና የሚመረተውን ሲኖቫክ የኮቪድ 19 ክትባት የማምረት ሂደት ውስጥ መግባቱንም ሚኒስትሯ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሯ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከቻይና ልኡካን ጋር በካይሮ ባደረጉት ውይይት የግብፁ ቫሴራ የክትባት አምራች ኩባንያ ለሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት የሚተርፍ ክትባት የማምረት አቅም እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ይህ የግብፅ ኩባንያ በአፍሪካ ያቻይናውን ሲኖቫክ ክትባት  ዋነኛ አምራች በመሆን እደሚያገለግል የገለፁት ሚኒስትሯ በዚህም ግብፅ የአፍሪካ ማእከል ትሆናለች ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በተስማሙት መሰረት እንደአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2021 መጨረሻ ላይ 40 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት የማምረት እቅድ መያዛቸውም ተሰምቷል፡፡ ከቻይና የመጡት ልኡካን የመጀመሪያው ዙር የ2 ሚሊዮን ክትባቶች እስኪመረቱ ለሶስት ሳምንታት በግብፅ እንደሚቆዩ አህራም ኦንላይን ዘግቧል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ሃላ ዛይድ አክለው እዳሉት ግብፅ አስትራዜኒካ ክትባትንም በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት በማድረግ ላይ ናት፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *