ሐሰት፡ በአዲስ አበባ፣ መስቀል አደባባይ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች ላይ የደረሰ የሞት አደጋ የለም።
ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶችና በጸጥታ አስከባሪዎች መሃል በተፈጠረ አለመግባባት በሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ስለመድረሱ የተገኘ ማስረጃም ሆነ ዘገባ የለም። የአብይ አህመድ ወታደሮች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የገለፁ የኦሮሞ ልጆች ላይ በሰነዘረው ጥቃት ከ4 ሰወች በላይ ተገደሉ የሚለው የፌስቡክ ልጥፍ ሐሰተኛ ነው።
ልጥፉ “የፋሽስቱ አብይ አህመድ ወታደሮች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የገለፁ የኦሮሞ ልጆች ላይ በሰነዘረው ጥቃት ከ4 ሰው በላይ መገደላቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።” ይላል። የኢሬቻ በዓል ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ መስከረም 22 እና 23 በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እና በቢሾፍቱ
ከተማ ደግሞ የሆራ ሃር-ሰዲ ብዙ ሕዝብ በታደመበት ተከብሯል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የገዳ ስርአት አንዱ ሲሆን፡ ኢሬቻ ደግሞ በገዳ ሥርአት ውስጥ ከሚታቀፉ ስርአቶች መካከል ይመደባል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ የማኅበረሰቡ ባህላዊ መሪዎች።
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው ደሎሎ ቡዴና የሆራ ስፍራ ኢሬቻ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ሲከበር አባገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ታድሟል። በዚህ በዓል አከባበር በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ የሚጠይቁ ጥሪዎች ከታዳሚው ተሰምተዋል። ከማለዳው 12 ሰዓት ገደማ አባገዳዎች እና ሃዳ-ሲንቂዎች ከመስቀል አደባባይ የኢሬቻ ስርዓት ወደ
ሚከበርበት ደሎሎ ቡዴና በሚያመሩበት ወቅት በመግቢያ በሩ አከባቢ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች እና በጸጥታ አካላቱ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መጠነኛ መረጋገጥ ተስተውሏል፡፡
አባገዳዎቹ በዚው የኢሬቻ ስፍራ ስርዓቱን አከናውነው ከወጡም በኋላ በጭፈራቸው እና በተቃውሞ ድምጽ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙም ተደምጠዋል። ወጣቶች "ፍትህ ለሃጫሉ" የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት “ኢሬቻ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋፅኦ ያደረጋችሁትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸውም “የ2014 ዓ.ም ኢሬቻ በዓልን በደማቅ ሁኔታ አክብረናል። ኢሬቻ የምስጋና ፣ የዕርቅ እና የሰላም በዓል ነው። የፍቅር ፣ የይቅርታ እና የአንድነት በዓሉን በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋፅኦ ያደረጋችሁትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
“የሆራ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የኦሮሚያ ፖሊሲ ኮሚሽን ገለጸ” ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶችና በጸጥታ አስከባሪዎች መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መጠነኛ መረጋገጥ መድረሱ የተዘገበ ቢሆንም በሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ስለመድረሱ የተገኘ ማስረጃም ሆነ ዘገባ የለም። አርትስ ቲቪ የአብይ አህመድ ወታደሮች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የገለፁ የኦሮሞ ልጆች ላይ በሰነዘረው ጥቃት ከ4 ሰወች በላይ ተገደሉ የሚለውን የፌስቡክ ልጥፍ ተመልክቶ ሐሰተኛ
ሆኖ አግኝቶታል ፡፡
. . . . .
ይህ ልጥፍ በፌስቡክ እና በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የፔሳቼክ የእውነታ መርማሪዎች በተከታታይ የሚያደርጉት የመረጃ ማረጋገጥ እና የተሳሳተ መረጃን የማጋለጥ ተግባር አካል ነው::
እንደ ፔሳቼክ ያሉ ገለልተኛ ሶስተኛ ወገን የእውነት መርማሪ ድርጅቶች ከፌስቡክ እና የማህበራዊ ድረ ገጾች ጋር በመጣመር የሃሰት ዜናን መለየት እንዲያስችልዎ ይሰራሉ:: ይህን የምናደርገውም በየማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚመለከቱት ልጥፍ/ መረጃ መነሻቸውን በማያያዝ እና ጠለቅ ያለ ዕይታ እንዲኖርዎ በማድረግ ነው::
በፌስ ቡክ ላይ የሐሰተኛ መረጃ ወይም የተጭበረበረ የመሰልዎ አጋጣሚ አለ?እንግድያውስ በእዚህ መንገድ ጥቆማ መስጠት ይችላሉ::እንዲሁም ይህን ተጨማሪ ኢንፎርሜሽን በመጠቀም አጠራጣሪ መልዕክቶችን ለመለየት የፔሳቼክ መንገዶችን ማየት ይችላሉ::
ይህ የእውነታ ምርመራ በአርትስ ቲቪ የእውነት መርማሪ ረደኤት አበራ ተጽፎ በፔሳቼክ ም/አዘጋጅ ኤደን ብርሃኔ አርትኦት የቀረበ ነው::
አንቀጹ ለህትመት እንዲበቃ ያረጋገጠው ደግሞ የፔሳቼክ ዋ/አዘጋጅ ኤኖክ ናያርኪ ነው::
ፔሳቼክ የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የፋይናንስ መረጃ መርማሪ ተቋም ነው :: ካትሪን ጊቼሩ እና ጀስቲን አርንስቴን በተባሉ ሰዎች የተመሰረተ እንዲሁም በአህጉሪቱ ትልቁ የሲቪክ ቴክኖሎጂ እና የጋዜጠኝነት መረጃ ቋት አቅራቢ በኮድ አፍሪካ የተገነባ ነው:: እንደ ጤና : የገጠር ልማት እና የንጹህ ውሃ አቅርቦት በመሳሰሉ መስኮች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከመንግስት የሚጠበቁ አቅርቦቶች ላይ የተጨባጩን ዓለም እይታችንን ሊቀርጹ የሚችሉ በይፋ በሚሰራጩ የፋይናንንስ መረጃዎችን ዙርያ ህብረተሰቡ እውነተኛ መረጃን ማገናዘብ እንዲችል ለማገዝ የሚያስችል ድጋፍ ይሰጣል:: ፔሳቼክ ሚድያዎች የሚያቀርቡትን ጥንቅርም ይፈትናል:: የበለጠ መረጃ ለማግኘት pesacheck.org. ይጎብኙ::
ፔሳቼክ ኮድ ፎር አፍሪካ ከዶቼቬለ አካዳሚያ ባገኘው ድጋፍ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሚድያዎች እንዲሁም የሲቪክ ተቋማት ጋር በመተባበር ኢኖቬት አፍሪካ ፈንድ በሚለው መስመሩ የሚያቀርበው እንቅስቃሴ ነው::