loading
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአመራር ለውጥ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 አቶ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ፡፡ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው አቶ መስፍን የሃላፊነቱን ቦታ የተረከቡት፡፡ አቶ መስፍን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ የጥገናና ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም የኦፕሬሽን ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። በተቋሙ ውስጥ ላለፉት 38 አመታት በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቶ መስፍን አየር
መንገዱ አሁን ያለበትን የስኬት ጎዳና ይበልጥ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለሰባት ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመሩትን አቶ ግርማ ዋቄ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው ታውቋል። የቦርድ አባላቱን በአዲስ መልክ ያዋቀረው አየር መንገዱ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ አቶ ረታ መላኩ እና አቶ አለማየሁ አሰፋን የቦርድ አባል አድርጎ መድቧል፡፡ በህመም ምክንያት ስራቸውን የለቀቁት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከአስር ዓመት በላይ በሀላፊነት ባገለገሉበት ወቅት አየር መንገዱን በሁሉም መለኪያዎች በአራት እጥፍ እድገት እንዲያስመዘገብ አግዘውታል ተብሏል፡፡


አቶ ተወልደ ካስመዘገቧቸው ስኬቶች መካከል የተቋሙን ዓመታዊ ገቢ ከ1 ቢሊዮን ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ፣ አየር መንገዱ የነበሩት 33 አውሮፕላኖችን ወደ 130 ከፍ ማድረግ፣ 3 ሚሊዮን የነበረውን የተጓዦች ቁጥር 12 ሚሊዮን ማድረስ ይገኙበታል ሲል አየር መንገዱ በፌስቡክ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የአየር መንገዱ የቦርድ አመራርና አባላት፣ እንዲሁም መላው የድርጅቱ ሰራተኞች አቶ ተወልደ ገብረማርያም ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነው ጤናቸው እንዲሻሻልም መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *