loading
የወባ በሽታን ከሀገሪቱ ለማጥፋት ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ ሊተገብር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 የወባ በሽታን ከሀገሪቱ ለማጥፋት ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ ሊተገብር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡ የወባ ቀንን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ 75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑን ጠቅሰዋል።


52 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በእነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖር ተናግረዋል። በወባ ምክንያት በየዓመቱ የሚከሰተውን የህመምና የሞት መጠን በመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል። የወባ በሽታን እ.አ.አ በ2030 ከኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ ወደ
ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የመከላከል ሥራ የዓለም ጤና ድርጅትን ተቀባይነት ያገኘ አመርቂ ውጤት
መመዝገቡን ተናግረው፤ ይህን ውጤት ለማስቀጠል የሁሉም ተቋማትና ህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


የወባ በሽታን ለማጥፋት በተለይ ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ መተግበር አለበት ብለዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ229 ወረዳዎችና በ4 ሺህ 400 ቀበሌዎች ላይ ሰፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ከ25 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል፡፡ የአልጋ አጎበር ለሚያስፈልጋቸው ወረዳዎች በ2013 ዓ.ም ከ8 ሚሊዮን በላይ አጎበር የተሰራጨ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተያዘው ዓመትም 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን አጎበር ለማሰራጨትና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶችን ኬሚካል ለመርጨት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *