ለጋሽ አካላት በአፍሪካ ቀንድ ለምግብ እጥት ለተጋለጡ ወገኖች 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ፡፡
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2014 ለጋሽ አካላት በአፍሪካ ቀንድ ለምግብ እጥት ለተጋለጡ ወገኖች 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከ40 ዓመታት በላይ ታይቶ የማያውቅ የድርቅ አደጋ መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ ቁጥራቸው ከ15 ሚሊዮን የሚበልጥ ሰዎች ለከፋ የምግብ እጥረት አደጋ ተጋልጠዋል ነው የተባለው፡፡
የምግብ እጥረቱ የተከሰተው በሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ሲሆን እነሱም ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ ናቸው፡፡ ለጋሾቹ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሲሉ ወደ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ለማድረግ ቃል የተገባው ጄኔቫ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮና የአውሮፓ ህብረት የሲቪል ሰዎች ጥበቃና የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አስተባባሪነት የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ ከፍተኛ ተወካዮች በተገኙበት በተደረገ ውይይት ነው፡፡
በዚህ ወቅት በተደረገው ውይይት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለአራተኛ ተከታታይ ወቅት የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ ሚሊዮኖች ለርሃብ፣ ለስደትና ለተላላፊ በሽታ መጋለጥ እጣ ፋንታቸው መሆኑ ትኩረት ተደርጎበታል፡፡ በዚህ ወቅት በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ባጋጠመ የውሃ እና የግጦስ እጥረት 3 ሚሊዮን
የሚጠጉ እንስሳት የሞቱ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል ተብሏል፡፡
የተ.መ.ድ የሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ ሀላፊ ማርቲን ግሪፊትዝ በአፍሪካ ቀንድ በርካታ ሰዎች ዳግም ለድርቅ ርሃብ መጋለጣቸውን በመጥቀስ ሁላችንም ችግራችውን ልንጋራቸውና በ21ኛው ክፍለዘመን ለርሃብ ቦታ እንደሌለው ልናሳያች ይገባል ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺክ በበኩላቸው ከተፈጥሮ አደጋው በተጨማሪ በሩሲያና በዩክሬን መካከል የተከሰተው ግጭት ለምግብ አቅርቦት እንቅፋት መፍጠሩን በመግለጽ የቀጠናውን ህዝቦች አለንላችሁ ለማለት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል፡፡