ማንችስተር ዩናይትድ አርሰናልን ከኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ውጭ አድርጎታል
ማንችስተር ዩናይትድ አርሰናልን ከኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ውጭ አድርጎታል
የኢምሬት ኤፍ ኤ ካፕ የአራተኛ ዙር ጨዋታዎች ትናንት ተካሂደዋል፡፡
የኦሌ ጉናር ሶልሻዬሩ ማንችስተር ዩናይትድ ትናንት ምሽት ወደ ሰሜን ለንደን አቅንቶ የኡናይ ኢምሪውን አርሰናል በ3 ለ 1 ውጤት በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ለቀያይ ሰይጣኖቹ ጎሎቹን የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ቺሊያዊው አሌክሲስ ሳንቼዝ፣ ጄሴ ሊንጋርድ እና አንቶኒ ማርሽያል ከመረብ ማገናኘት ችለዋል፡፡ ሮሜሉ ሉካኩ ለሳንቼዝ እና ሊንጋርድ ጎሎች መቆጠር ምክንያት ሲሆን የጨዋታው ኮከብ ተሰኝቷል፡፡
ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ አርሰናል 2 ለ 0 እየተመራ ባነበረበት ወቅት ግብ በማስቆጠር ቡድን ተስፋ ቢዘራበትም ከሽንፈት ግን ሊታደገው አልቻለም፡፡
በዚህም ሶልሻዬር በተቀናቃኝ ክለብ አርሰናል ላይ በሁሉም ውድድር ስምንተኛ ተከታታይ ድሉን ማሳካት ችሏል፡፡ በአርሰናል በኩል የተከላካዮቹ ሶቅራጥስ ፓፓስታቶፑለስ እና ሎረን ኮሸልኒ ጉዳት ያስተናዱ ሲሆን ይህ ዜና ለአሰልጣኝ ኢምሪ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡
ትናንት ምሽት በተከናወነ ሌላ ግጥሚያ ብሪስቶል ሲቲ ቦልተን ዋንደረርስን 2 ለ 1 ረትቷል፡፡
የኤፍ ኤ ካፕ የአራተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ በርካታ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ፤ ከነዚህም መካከል ምሽት 12፡00 ላይ ማንችስተር ሲቲ በኢቲሃድ ከ በርንሊ፣ ብራይተን በአሜክስ ከ ዌስት ብሮሚች አልቢዮን እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ከ ዋትፎርድ የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዕሁድ ምሽት 1፡00 ላይ ክሪስታል ፓላስ በሴልህረስት ፓርክ ከ ቶተንሃም እንዲሁም 3፡00 ቼልሲ ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ ከሸፊልድ ዌንስዳይ ይገናኛሉ፡፡