ሱዳናዊያን በሀገሪቱ የስልጣን መጋራት ስምምት የተደረገበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ሰልፍ አካሂደዋል::
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 12፣ 2012 ሱዳናዊያን በሀገሪቱ የስልጣን መጋራት ስምምት የተደረገበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ሰልፍ አካሂደዋል::
ነዋሪዎቹ ካርቱም ውስጥ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ አሁን ባለው የሉዓላዊ ምክር ቤት አስተዳደር ቅሬታ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡ ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት ፕሬዚዳንት አልበሽርን በሃይል ከስልጣናቸው ያስወገዱት ጄኔራሎችና ህዝቡን ወክለው ስልጣን የተጋሩት ፖለቲከኞች ሀገር መምራት ከጀመሩ አንድ
ዓመት ቢያስቆጥሩም የተፈለገው ለውጥ አልመጣም በማለት ነው፡፡ የሱዳንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት
ሱዳናዊያን በአስቸኳይ የፖለቲካ ሪፎርም እንዲደረግ ጠይቀዋል ነው የተባለው፡፡
አፍካ ኒውስ እንደዘገበው ተቃዋሚዎቹ በመንግስት ካቢኔ ምክር ቤት ዋና ቢሮ ፊት ለፊት ተሰባስበው ባለ ስልጣናቱ ጥያቄዎቻቸውን በዝርዝር እንዲሰሟቸው ቢጠይቁም ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ በትኗቸዋል፡ፖሊስ ሰልፉ ሰህጋዊና ሰላማዊ ነበር የሚል መግለጫ ቢሰጥም ግጭት ተፈጥሮ የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን በመናገር ለዚህም የካርቱም አስተዳዳሪ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ ከካርቱም ውጭ በኡምዱርማን እና ሌሎች በርካታ ከተሞችም መካሄዱን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡