loading
ስራውን ቆጥሮ ያስረከበው ምክር ቤት ውጤቱን በአግባቡ ቆጥሮ ይረከብ ይሆን?

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቆጥሮ የሰጠውን ስራ ቆጥሮ መረከብ የሚያስችለውን የፊርማ ስነስርዓት አከናወነ፡፡ ምክር ቤቱ አስፈፃሚውን የመከታተልና መቆጣጠር ስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ብሎም የተጠያቂነትን ስርዓት ለማስፈን ይረዳው ዘንድ ነው ይህን ያደረገው፡፡


ሥምምነቱ በዋናነት በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና በአስፈፃሚዎች (የቢሮ ሃላፊዎች) መካከል የተቋማቱን እቅድ መሰረት ያደረገ ይዘት ያለው ሲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በተገኙበት የፊርማው ስነስርዓት ተካሂዷል፡፡ ይህ ከተቋማት ሀላፊዎች እና አስፈጻሚ አካላት ጋር የተደገረው የፊርማ ስነስርዓት ቀዳሚ ዓላማ ስራን ቆጥሮ ሰጥቶ ቆጥሮ የመረከብ አሠራር ስርዓትን ተግባራዊ የሚያደረግ ነው፡፡

በዚህም ምን ተግባር፣ መቼ እና በምን ያህል በጀት እንደሚከናወን ቀድሞ አውቆ ክትትል ለማድረግና ሪፖርት ለመጠየቅ የሚያመች፣ እንዲሁም ለአስፈጻሚው ምክር ቤት አባል ልክ እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ የሚያገለግል ነው ተብሏል፡፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፊርማው ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ይህ ስምምነት ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓላማ ያለውና ስራን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነው፡፡


ምክር ቤቱና ሕዝባችን የጣለብንን ኃላፊነት በተሟላ መልኩ እንድንፈጽም የሚያስችል የተጠያቂነት ስርዓትን ከንግግር ባለፈ መሬት ላይ ለማውረድ የሚረዳ፣ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንድናቀርብ የሚያስችለን ነውም ብለዋል፡፡ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የህዝብ ተወካዮች አስፈፃሚውን በየጊዜው በመከታተልና በመደገፍ የከተማዋን እድገትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ሊሰሩ ይገባል ነው የተባለው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *