loading
ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ ከሜዳቸው ውጭ የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ ከሜዳቸው ውጭ የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ትናንት መካሄድ ጀምረዋል፤ ደቡብ ፖሊስ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ የ 1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት ነጥብ እንዲያሳካ ያደረገችውን ብቸኛ ጎል የፖሊሱ ተጫዋች ሙሉዓለም ረጋሳ ነው በራሱ ግብ ላይ ማስቆጠር የቻለው፡፡ ይህን ተከትሎ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ መጠን ወደ 12 ማሳደግ ችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ መከላከያ ከ አዳማ ከተማ ተጫውተው፤ እንግዳው አዳማ በ5 ለ 1 ሰፊ ውጤት መርታት ችሏል፡፡ አዳማ በበረከት ደስታ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ቢችልም፤ ምንይሉ ወንድሙ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ጦሩን አቻ አድርጓል፤ የመጀመሪያው አጋማሽ በአንድ አቻ ውጤት ቢጠናቀቅም ከዕረፍት መልስ አዳማዎች በዳዋ ሁቴሳ አራት ተከታታይ ግቦች አማካኝነት ከሜዳቸው ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በግብ ተንበሻብሸው አሸንፈዋል፡፡
ዛሬ ሶስት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ በትግራይ ስታዲየም ደደቢት ከ ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከነማ ከ ባህር ዳር ከነማ በተመሳሳይ 9፡00 ሲጫወቱ፤ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም 10፡00 ሲል ከ ስሑል ሽረ ይገናኛሉ፡፡
ዕሁድ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ስታዲየም ፋሲል ከነማን ሲያስተናድ፤ ሰኞ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ሀዋሳ ከነማ ከ ጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም ትግራይ ስታዲየም ላይ መቐለ 70 እንደርታ ከ ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 9፡00 ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሊጉን ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብ ሲመራ ሀዋሳ ከነማ በ14 ይከተላል፤ ሲዳማ ቡና በ13 ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህር ዳር ከነማ በዕኩል 12 ነጥቦች አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የአዳማው ዳዋ ሁቴሳ፣ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ እና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በዕኩል 6 ጎሎች ይመሩታል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *