በሀገሪቱ የሳይበር ጥቃት ከተቃጣባቸው ተቋማት የሚዲያ ተቋማት በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 በሀገሪቱ የሳይበር ጥቃት ከተቃጣባቸው ተቋማት የሚዲያ ተቋማት በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ከማንኛውም የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው እና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ስምምነቱን ፈርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሃን ከሚደርስባቸው የሳይበር ጥቃት ለመከላከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በ2012 ዓ.ም በሀገሪቱ የሳይበር ጥቃት ከተቃጣባቸው የፋይናንስ ተቋማት ቀጥሎ የሚዲያ ተቋማት በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ኤጀንሲው የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ሃላፊነት ይውሰድ እንጂ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ትኩረት የሚያሻው መሆኑንም አብራርተዋል።የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው የዘመኑ ውጊያ በቴክኖሎጂ በመሆኑ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን መረጃን በትክክል ተደራሽ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው ለዚህም ከሳይበር ጥቃት ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መዘዋወር ይገባቸዋል ብለዋል።