በስደት የምቀር እንጂ ወደምወዳት አገሬ የምመለስ አይመስለኝ ነበር አሉ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ
በስደት የምቀር እንጂ ወደምወዳት አገሬ የምመለስ አይመስለኝ ነበር አሉ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ
አርትስ 28/02/2011
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ትላንት ከኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ጋር ተገናኝተዋል ::
ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ከ 32 ዓመት በኃላ የቀድሞ መስሪያ ቤታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው እንኳን ለሀገርዎ አበቃዎት፣ወደ ቀድሞ መስሪያ ቤትዎም በሰላም መጡ ብለዋቸዋል፡፡
ከ32 ዓመታት ስደት በኃላ አገራቸው የተመለሱት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ በአገራችን ታሪክ ውስጥ 20ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ዶከተር ወርቅነህ ደግም 27ኛ፡፡
ዶክተር ወርቅነህ ተቀብለው ማነጋገር ብቻ ሳይሆን የኮለኔል ጎሹን የቀድሞ ቢሮ ያስጎበኙ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመካሄድ ላይ ያለውን የማስፋፍያ ግንባታም ራሳቸው ወስደው አስጎብኝተዋቸዋል፡፡
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ዶክተር ወርቅነህ አስታውሰው እሳቸውን በቀድሞ ቢሯቸው በመቀበላቸው ክብር እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ትውልድ የቀድመውን ፈለግ መከተል እና ማክበር ይገባዋል ያሉት ዶከተር ወርቅነህ ዜጋ አገሩን እየወደደ እና እየናፈቀ ስደተኛ የሚሆንበት ዘመን በዚህ ትውልድ ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በበኩላቸው በዛው በስደት የምቀር እንጂ ወደምወዳት አገሬ የምመለስ እንዲሁም ይህ ጊዜ የሚመጣ አይመስለኝ ነበር ሲሉ በሞቀ ፈገግታ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በአንክሮ እንደሚከታተሉ የተናገሩት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት የአፍሪካ ቀንድን የሰላም ሁኔታ ለመለወጥ መስሪያቤቱ ያደረገውንዲፕሎማሲ አደንቃለሁ ብለዋል፡፡
እሳቸውም በቀረው ዘመናቸው መስሪያ ቤቱንም ሆነ በአገሪቱ እየተጠናከረ ያለውን የለውጥ ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በውይይታቸው ማሳረጊያም አገር የመምራት ኃላፊነት በትውልዶች ቅብብል የሚከናወን ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞየማንም ሳትሆን የሁላችንም ናት ብለዋል፡፡