በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 1ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባት ለመከተብ ዘመቻ ተጀመረ፡፡
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 18፣2013 በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 1ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለመከተብ ዘመቻ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ አስታወቁ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮቪድ -19 ስርጭት በርብርብ መግታት ካልተቻለ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ዮሐንስ እንደገለጹት ባለፉት አራት ሳምንታት በኮቪድ -19 የመያዝ ምጣኔው፣ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር እና በበሽታው ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ አድርገው ስርጭቱን መግታት ካልተቻለ በሽታው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ተብሏል፡፡
የስርጭቱን መጨመር ተከትሎ በመመሪያ ቁጥር 30 የነበሩ ክልከላዎችን የሚያስቀጥልና አንዳንድ ማሻሻያዎችን ያካተተ የተሻሻለ የኮቪድ -19 መከላከል መመሪያ ቁጥር 803/2013 ይፋ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መመሪያውን ተግባራዊ
በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
የሚደረገው ቅድመ ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ስርጭቱን ለመከላከል አንዱና ዋነኛው መፍትሄ የኮቪድ- 19 ክትባት መውሰድ ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ÷ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 1ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለመከተብ ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ክትባቱ በሁሉም የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች ስለሚገኝ ማንኛውም እድሜው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ ዜጋ ክትባቱን በነጻ መውሰድ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡