በኢሮፓ ሊግ አርሰናል እና ቼልሲ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል
በኢሮፓ ሊግ አርሰናል እና ቼልሲ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል
አርትስ ስፖርት 30/02/2011
ትናንት ምሽት በርካታ የኢሮፓ ሊግ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን ወደ ጥሎ ማለፉ የተሻገሩ ቡድኖች መለየት ጀምረዋል፡፡ ወደ ቤላሩስ ያቀናው ቼልሲ ከባቴ ቦሪሶቭ ጋር ጨዋታውን አድርጎ በፈረንሳያዊው ኢሊቪየር ጅሩ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 በመርታት ምድቡን በ12 ነጥብ እየመራ ከወዲሁ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ ምድቡ ውስጥ ሞል ቪዲ ፓኦክ ሳሎኒካን 1 ለ 0 በማሸነፉ በ6 ነጥብ ይከተላል፡፡ በኡናይ ኢምሪ የሚሰለጥነው አርሰናል ደግሞ ኢምሬትስ ላይ የፖርቱጋሉን ስፖርቲንግ ሊዝበን አስተናግዶ ያለምንም ግብ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ደምድሟል፡፡ ነገር ግን መድፈኞቹ ምድቡን በ10 ነጥቦች እየመሩ 32ቱን የጥሎ ማለፍ ቡድኖች ተቀላቅለዋል፡፡ በጨዋታው እንግሊዛዊው ዳኒ ዌልቤክ ጉዳት አስተናግዶ በቃሬዛ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሪ ተጫዋቹ ሆስፒታል እንደሚገኝ ገልፀው የጉዳቱን መጠን ለማወቅ እየጠበቅን ነው ያሉ ሲሆን ከባድ ጉዳት ሊሆን እንደሚችል ግን ጠቁመዋል፡፡ በምሽቱ በተደረጉ ሌሎች ግጥሚያዎች መካከል ወደ ስፔን ያቀናው ኤስ ሚላን ከሪያል ቤቲስ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል፡፡ ባየር ሊቨርኩሰን ዙሪክን 1ለ 0 ያሸነፈ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ከምድብ A ተያይዘው ወደ ተከታዩ ዙር አቅንተዋል፡፡ ሲቪያ 3 ለ 2 አኪሳርስፖር፣ ዳይናሞ ኬቭ 3 ለ 1 ሬን፣ ሴልቲክ 2 ለ 1 አር.ቢ ላይፕዚህ፣ ቦርዶ 1 ለ 1 ዚነት፣ ፌነርባቼ 2 ለ 0 አንደርሌክት፣ ስፓርታክ ሞስኮው 4 ለ 3 ሬንጀርስ፣ ላዚዮ 2 ለ 1 ማርሴ፣ አፖሎን ሊማሶል 2 ለ 3 ኢንትራክት ፍራንክፈርት በሆነ ውጤት ተለያይተዋል፡፡