loading
በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ 11 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ::

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9 ፣2012  በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ 11 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ:: ምእራብ አፍሪካዊቷ ሪፓብሊክ ኮንጎ በአሁኑ ጊዜ ሶስት ትላልቅ ፈተናዎች ከፊቷ ተጋርጠውባታል ነው የተባለው፡፡ አንደኛው የመላው ዓለም ችግር የሆነው የኮሮና ቫይረስ፣ ሁለተኛው ደጋግሞ ያንገላታት የኢቦላ ቫይረስ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከኩፍኝ ወረርሽኝ ጋርም እየታገለች ነው፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው በዲሞክራቲክ ኮንጎ በቅርቡ ዳግም ባገረሸው የኢቦላ ቫይረስ በሳምንቱ መጨረሻ 17 ሰዎች መያዛቸው ሲረጋገጥ ከነዚህም መካከል አስራ አንዱ ሞተዋል፡፡ የሀገሪቱ የብሄራዊ ባዮሜዲካል ምርምር ተቋም ባወጣው ሪፖርት ከአሁን ቀደም በቀን 14 ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸው መታወቁ የሥርጭቱ መጠን ከፍ እያለ መምጣቱን ያሳያል ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ ኢኮየተር በተባለው የኮንጎ ግዛት ከሰባት የበሽታው ስጋት ከተባሉ ዞኖች ከ2 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን አመላክቷል፡፡ ሀገሪቱ ይሄ ሁሉ ችግር ሳይበቃት በተለያዩ ግዛቶቿ እየተባባሰ የመጣው የእርስበርስ ጦርነት አላላውስ ብሏታል፡፡ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ኢቦላን ከምድሯ ለማጥፋት ተቃርባ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳግም መከሰቱ ከሌሎች ችግሮቿ ጋር ተዳምሮ ትልቅ ጫና ፈጥሮባታል ተብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *