ባርሴሎና የኮፓ ዴል ሬይ የመልስ ጨዋታ በድል ተወጥቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተቀላቅሏል
ባርሴሎና የኮፓ ዴል ሬይ የመልስ ጨዋታ በድል ተወጥቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተቀላቅሏል
የስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ግጥሚያዎች ትናንት ምሽት ተከናውነዋል፡፡
ካምፕኑ ላይ ሲቪያን ያስተናገደው ባርሴሎና 6 ለ 1 ሲረታ፤ በአጠቃላይ ውጤት 6 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የግማሽ ፍፃሜ ዙር ተቀላቅሏል፡፡
ባለፈው ሳምንት አንዳሉዥያ ላይ የ2 ለ 0 ሽንፈት ተከናንቦ የተመለሰው ባርሳ፤ ምናልባት ባለፉት አራት አመታት ከነገሰበት የንጉስ ዋንጫ መድረክ በቀላሉ ሊሰናበት ይችላል ቢባልም ፤ አሰልጣኝ ኤርኔስቶ ቫልቬርዴ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች በማሰለፍ ውጤቱን ቀልብሰዋል፡፡
ፊሊፔ ኮቲንሆ እና ሊዊስ ሱዋሬዝ በምሽቱ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ፤ ተከላካዩ ሰርጂ ሮቤርቶ እንዲሁም ራሱ ተጠልፎ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት፤ ለኮቲንሆ አሳልፎ የሰጠው ሊዮኔል ሜሲ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ የካታላኑ ቡድን ከዚህም የላቀ የግብ መጠን ሊያስቆጥር ቢችልም የሲቪያው ግብ ጠባቂ ያስፐር ሲልሰን ግን አምክኗቸዋል፡፡
አራና ሎፔስ ደግሞ ለሲቪያ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ትናንት ምሽት አስቀድሞ በስታዲዮ ቪያማሪን ሪያል ቤቲስ ኢስፓኞልን 3 ለ 1 ሲረታ፤ በድምር ውጤት 4 ለ 2 ድል በማድረግ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡
ቫሌንሲያ፣ ባርሴሎና እና ሪያል ቤቲስ እስካሁን ግማሽ ፍፃሜውን የተዋሀዱ ቡድኖች ሲሆን ዛሬ ምሽት ጅሮና በስታዲዮ ሙኒሲፓል ዴ ሞንቲሊቪ ሪያል ማድሪድን ይገጥማል፤ ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ቤርናባው ላይ ተገናኝተው በማሪድ 4 ለ 2 አሸናፊነት ተለያይተዋል፡፡