loading
ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና ጃዊ አካባቢ የነበረው የፀጥታ ችግር ወደ መረጋጋት መመለሱ ተገለፀ፡፡

ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና ጃዊ አካባቢ የነበረው የፀጥታ ችግር ወደ መረጋጋት መመለሱ ተገለፀ፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ዛሬ ለሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ከሚያዝያ 17 ቀን ጀምሮ የነበረው የፀጥታ መደፍረስና በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በግለሰቦች የተነሳ ግጭት አድጎ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉንና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት በጋራ በመሥራታቸው አንጻራዊ ሠላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡

የግጭቱን ዝርዝር ሁኔታ ለማጣራት የሁለቱ ክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ እንደሆኑና ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት በሁለቱም ወገን የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉን፣ ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል፤ ድርጊቱ በክልሉ መንግሥት በጥብቅ የሚወገዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ጃዊ ወረዳ ሚያዝያ 21 ቀን 2011ዓ.ም ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የሰው ሕይወት ማጥፋታቸውን የገለጹት አቶ አሰማኸን ‹‹የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን እያጣራ ነው፤ ጥፋትን በጥፋት የመመለስ አጀንዳ ሊታረም ይገባል›› ብለዋል፡፡

የአማራና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተከትሎ በአካባቢዎቹ አሁን ላይ አንጻራዊ መረጋጋት መፈጠሩንም ነው ለመገናኛ ብዙኃን ያስረዱት፡፡
ከኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኅብረተሰቡ ጋር የሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ አመራሮች ቦታው ድረስ በመገኘት የማጣራትና የማረጋጋት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

‹‹የአጣሪ ቡድኑ የሟቾችንና ተጎጂዎችን እንዲሁም ሌሎች የጉዳት መጠኖችን አጣርቶ እንደደረሰ ለሕዝብ እናሳውቀለን›› ያሉት አቶ አሰማኸን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የሚገለጹ ቁጥሮች የተሳሳቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ አብመድ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *