ቻይና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ትተገብረው የነበረውን የሁለት ልጅ ፖሊሲ ልታሻሽል ነው፡፡
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23፣ 2013 ቻይና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ትተገብረው የነበረውን የሁለት ልጅ ፖሊሲ ልታሻሽል ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረገው የሺንዋ ዘገባ መንግስት ጥንዶች ሶስት ልጆችን እንዲወልዱ ሊፈቅድ መሆኑን ያመለክታል፡፡መንግስት ከዚህ በፊት ጥንዶች ሁለት ልጆች ብቻ እንዲኖራቸው የሚያስገድድውን ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አሁን ላይም ይህን ፖሊሲ በመቀየር ጥንዶች ሶስት ልጆችን እንዲወልዱ የሚፈቅደው የውሳኔ ሃሳብ በሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ መጽደቁን ዘገባው አመላክቷል፡፡ የአሁኑ ውሳኔ ባለፉት አስር አመታት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የሃገሪቱ የህዝብ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል፡፡
አሁን ላይ በሃገሪቱ ያለው የውልደት ምጣኔ ከ1960ዎቹ ወዲህ ዝቅተኛ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡ ባለፈው አመት የተደረገ ጥናትም በቻይና 12 ሚሊየን ህጻናት መወለዳቸውን ያመላክታል፤ ይህም በፈረንጆቹ 2016 ከተወለዱት 18 ሚሊየን ህጻናት አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ቻይና በፈረንጆቹ 1979 የህዝብ ቁጥሯን ለመቀነስ በሚል የአንድ ልጅ ፖሊሲን ያስተዋወቀች ሲሆን በፈረንጆቹ 2016 ደግሞ ፖሊሲዋን ቀይራ የሁለት ልጅ ፖሊሲን አስተዋውቃ ነበር፡፡