አርትስ ዝክረ አደዋ አደዋ ድላችን አደዋ መኩሪያችን ዛሬ እያንዳንዳችን ለያዝነዉ ማንነታችን መነሻ ነዉ፡፡
አርትስ ዝክረ አደዋ
አደዋ ድላችን አደዋ መኩሪያችን ዛሬ እያንዳንዳችን ለያዝነዉ ማንነታችን መነሻ ነዉ፡፡
ታዲያ ለዚህ ታላቅ አፍሪካዊ ድላችን አባቶቻችን በባዶ እግራቸዉ በኋላ ቀር የጦር መሳሪያ ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለዋል፡፡በንጉስ ሚኒሊክ መሪነት ጦርነቱ ቢካሄድም ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ከያሉበት ተጠራርተዉ በማንነታቸዉ ላይ የመጣዉን ወራሪ ድል ነስተዋል፡፡
አርትስ በአደዋ ላይ የዘመቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያን መዘከር ባይችልም በየአካባዉ የነበሩ የጦሩ መሪዎችን ታሪክ በተከታተይ ያቀርባል፡፡
የዛሬዉ የአርትስ አደዋ ተዘካሪ የወሎው ንጉሥ ራስ ሚካኤል አሊ ናቸዉ
የወሎዉ ንጉሥ ራስ ሚካኤል በሶስቱም አዉደ ዉጊያዎች በመሳተፍ ታሪክ ሊዘነጋዉ የማይገባ ድል አድርገዋል፡፡
ራስ ሚካኤል አሊ ጠንካራ እና በቁጥር ብዙውን የጦር ሰራዊት በመገንባታቸው ይታወቃሉ፡፡
ከራስ ሚካኤል ጦር በቀር በሶስቱም አዉደ ዉጊያ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ጦር አለመኖሩ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ለዚህም ነዉ ራስ ሚካኤል በአድዋ ዘመቻ ግንባር ቀደም ከነበሩት ዘማቾች እና በአድዋ ጦርነት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ እንደሆኑ ታሪክ የሚዘክራቸው ፡፡
ፈቃዱ በኛ የተባሉት የታሪክ ፀሀፍት የራስ ሚካኤል ጦር በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ቁጥሩ 70 ሺህ ደርሶ እንደነበር ፅፈዋል፡፡
ይህንን ጦር በጀግንነት በመምራት የአድዋ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በተለይም ራስ ሚካኤል በአድዋ ጦርነት የተጫወቱት ሚና ደማቁ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
ከአድዋ በፊት የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት አምባላጌ ላይ ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤልና የራስ መንገሻ ጥምር ጦር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተራራዉን ከቦ ከተዋጋ በኋላ የጣልያንን ጦር መሪዉን ሜጀር ቶሰሊን መግደል ችሏል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ራስ ሚካኤል በአምባላጌዉ ጦርነት 15 ሺህ ጦር በማሰለፍ አኩሪ ታሪክ እንደሰሩ ፅፈዋል፡፡
በአድዋ ጦርነት ወቅት በጄኔራል ኦሬስቴ ባራቲየሪ ፊት አውራሪነት የተመራዉ የጣልያን ጦር ወረራ ያካሄደው በሶስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ወደ አደዋ የዘመቱትን የጦር አዝማቾችና ያዘመቱትን የሠራዊት ብዛት በተመለከተ ከንጉሠ ነገሥቱ በመቀጠል ሁለተኛ የሚባለዉን የሠራዊት ብዛት ይዘዉ የዘመቱት ራስ ሚካኤል እንደነበሩ ታሪክ መዝግቧል፡፡
ይኸውም ፤ከወረኢሉ እስከ ትግራይ ድረስ በአጠቃላይ ለ150,000 ጦር ምግብ እና መጠጥ ያቀረበው የወሎ ህዝብ እና ንጉስ ሚካኤል አሊ ናቸው ሲል እንግሊዛዊዉ የታሪክ ፀሃፊ አስፍሯል፡፡
እንዲህ ባለ ሁኔታ የጣልያን ጦር የካቲት 22 ቀን ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋጋ ሲል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አድዋ ጦር ግንባር ደረሰ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ታላቁ የአድዋ ጦርነት ተጀመረ፡፡
በዚህ ጦርነት በመካከለኛዉ ግንባር ራስ ሚካኤል ከትግል አጋሮቻቸዉ ጋር በመሆን ከጠላት ጦር ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀዉ በአሪሞንዲ የተመራዉን ጦር ድል ማድረጋቸውን እና የጣሊያኑን ጦር መሪም ጄኔራል አሪሞንዲም በዚሁ ጦርነት መሞቱን ታሪክ ያሳያል፡፡
የራስ ሚካኤል ሚና በዚህ የተገደበ አልነበረም፡፡ ከዳቦር ሚዳ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሲፋለም የነበረዉ የራስ አሉላ ጦር ከፍተኛ ጫና ላይ ስለነበር አፄ ምኒልክ የራስ ሚካኤል ጦር ወደስፍራዉ ሄዶ እንዲያግዝ ትዕዛዝ በሰጡበት ወቅትም ከዳቦር ሚዳ ተናንቆ የነበረዉን የራስ አሉላን ጦር ለማገዝ ወደ ግራ ግንባር ተንቀሳቀሰ፡፡
በዚህን ጊዜ ወታደሮቻቸው ፤
ማን በነገረዉ ለጣሊያን ደርሶ
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ ፤ ሲሉ የፉከራ ዜማን አዜሙ፡፡
እንዲህ ባለ ሁኔታ የአሉላና እና የሚካኤል ጦር የጠላትን ጦር አሸንፎ ጄኔራሉን ዳቦር ሚዳን ገድሏል፡፡
ጥምር ጦሩ እኩለ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ የጣሊያንን ጦር ደመሰሰ፡፡ መሪዉን አልበርቶኔንም ማረከ፡፡ ጦርነቱ በግማሽ ቀን ዉስጥ በኢትዮጵያዉያን ድል አድራጊነት ሲጠቃለል ሀምሳ ስድስቱም የጣልያን መድፎች፣ በርካታ ከባድና ቀላል መትረየሶች እንዲሁም ጠመንጃዎች ተማርከዋል፡፡
ከእነዚህም ወስጥ በራስ ሚካኤል የተማረኩት በደሴ ሙዚዬም ይገኛሉ፡፡
ክብርና ሞገስ ለወሎው ንጉሥ ራስ ሚካኤል አሊ
በ ሰላም ገብሩ ተዘጋጀ